በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ቅዱሳን፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ
ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ብሔራዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳንን በቅድስናቸው፣ ጻድቃንን በጻድቃንነታቸው፣ ሰማዕታትንም በሰማዕትነታቸው አምና ተቀብላ ዘለዓለማዊ ምስክርነቷን በአፍ በመጣፍ ትመሰክራለች ፤ አማላጅነታቸውንም ትቀበላለች፡፡
ይሁን እንጂ ስለ ቅዱሳኑ ዝርዝር መግልጫ ከመግለጻችን አስቀድሞ ሀገረ እግዚአብሔር ስለሆነችው ኢትዮጵያ ሀገራችን በመጠኑም ቢሆን ማውሳቱ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም “ በስመ ኀዳሪ ይጼዋዕ ማኅደር፣ ወበስመ ማኅደር ይጼዋዕ ኀዳሪ” እንደሚባለው በነዋሪው መኖሪያው፣ በመኖሪያውም ነዋሪው ይጠራል ማለት ሲሆን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” በማለት የተነበየውን ትንቢት የተናገረውን ትምህርት በጥልቀት ስንመረምር ልዑል እግዚአብሔር ከኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያም ከልዑል እግዚአብሔር እስከ ሕልቀተ ዓለም የማይነጣጠሉ መሆናቸውን የምናይበት ረቂቅ ምሥጢር ነው፡፡ (መዝ 67፡31)
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሦስት ሺህ ዓመታት የበለጠ የነጻነት እድሜ የተቆጠረላት፣ በእርግጥም ሀገረ አምላክ ናት፣ በመሆኑም ሀገራዊ የሆነ ወግና ሥርዓት ያላት ስትሆን ብሉይ ኪዳንንና ሐዲስ ኪዳንን መሠረት ያደረገ ከማንም ያልተከለሰና ያልተበረዘ ንጹሕ እምነትና ሥርዓተ አምልኮት ያላት ሉዓላዊት ሀገር ናት፡፡
* ቅድስና፡- ቅድስና በምንልበት ጊዜ
ሀ. የባሕርይ ቅድስና፤
ሊ የጸጋ ቅድስና፣ ብሎ በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡
የባሕርይ ቅድስና በምንልበት ጊዜ ለእግዚአብሔር ብቻ የምንገልጸው ልዩ አገላለጽ ነው፡፡ የጸጋ ቅድስና
በምንልበት ጊዜ ደግሞ ሰማያውያን መላእክትና ምድራውያን ሰዎች ማለትም ጻድቃን፣ ሰማዕታት ራሳቸውን
ለቅድስና አዘጋጅተው ሲገኙ ቅድስናውን የሚያገኙት የቅድስና ባለቤት ከሆነው ከእግዚአብሔር የሚገኝ ልዩ
ስጦታ ቢሆንም የራስንም ጥረትና ተጋድሎ የሚጠይቅ መሆኑም አይካድም፡፡ በተለይ ምድራውያን ሰዎች
በሃይማኖት ጸንተው፣ በበጎ ሥራ ተቃኝተው በቅን ልቡና በትሁት ሰብእና እግዚአብሔርን ሲያገለግሉ ቅዱሳን
ይሆናሉ ፤ ቅዱሳንም ይባላሉ፡፡ “ እኔ አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎአልና ነው፡፡ (ዘሌ
19፡2፤ 1ኛ ጴጥ 1፡15-17) ፡፡
ጻድቃን፡- ጻድቃን የሚባሉት ደግሞ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃ ሰማዕታት በሙሉ በዱር፣ በገደል፣ በእሳት፣ በስለት፣ በረሃብ፣ በእርዛት፣ በጾም፣ በጸሎት፣ ከባ እድ ከዘመድ ርቀው ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን በማወጅ እና በማስተማር ጌታ በወንጌል “በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” (ማቴ 24 ፡ 9) ሲል እንደተናገረው በምናኔ የተንገላቱ ስለ ስሙ መከራ የተቀበሉ ፣ ለእምነታቸው፣ ለምግባራቸው፣ ለባህላቸውና ለሥርዓታቸው ከሀገር ወደ ሀገር፣ ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወሩ ስለ ክርስትና ሃይማኖት የተዋጉትና የተጋደሉት ሁሉ ጻድቃን ሰማዕታት ይባላሉ፡፡
በዋቢነት የሚጠቀሰውም “ ስለ ጌዴዎን፣ ስለባርቅ፣ ስለ ሳምሶን፣ ስለ ዮፍታሔ፣ ስለ ዳዊት፣ ስለ ሳሙኤል፣ ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥረኛል፤ እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነ፤ ጽድቅ የሆነውን ነገር አደረጉ ፤ የተሰጣቸውን ተስፋ አገኙ፤ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ ፤ ከደካማነት ወደ ብርቱነት ተለወጡ ፤ በተጋድሎ ኃይለኞች ሆነ ፤ የጠላትን ወታደሮች አባረሩ፤ ሌሉችም የበለጠ ትንሣኤን ለማግኘት አስበው ተደበደቡ፣ ከእስራት ነጻ መሆንንም እንቢ አሉ ሌሎች መዘባበቻ ሆነው ተገረፉ፤ ሌሉች በእግር ብረት ታስረው ወደ ወህኒ ቤት ተጣሉ ፤ በድንጋይ ተወገሩ ፤ በመጋዝ ተሰነጠቁ፣ በሰይፍ ተገደሉ፤ የበግና የፍየል ቆዳ ለብሰው ተንከራተቱ፣ ድሆችና ስደተኞች ሆነው ተንገላቱ፣ ዓለም ለእነርሱ ተስማሚ ሆና ስላልተገኘች በበረሃ፣ በተራራ፣ በምድር ውስጥ ባሉ ዋሻዎችና ፈፋዎች ዞሩ፡፡” (ዕብ 11፡32-39) የሚለው ቃለ ሐዋርያ ነው፡፡
ሰማዕታት፡- ሰማዕታት ማለት ታማኝ ምስክሮች ማለት ሲሆን ስለ ሀገርና ስለወገን፣ ስለነጻነትና ስለእምነት (ሃይማኖት) በአጠቃላይ ስለ ቤተ ክርስቲያንና ስለ ወንጌል ቃል መስፋፋት በአደባባይ ቆሞ ታማኝ ምስክርነትን መግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ ፤ በሰው ፊት የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ” ሲል ያስተማረው፡፡ (ማቴ 10፡32-33)
ቅዱሳን ሰማዕታት ከሚባሉት ዐበይት ሰማዕታት አንዱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘልዳው ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ አባቱ አንስጣቴዎስ (ዘሮንቶስ) ሲባል እናቱ ደግሞ ቴዎብስታ ትባላለች፡፡ የተወለደውም ጥር 2 ቀን 277 ዓ.ም ቀጰዶቅያ በምትባለው በትንሹ ምሥራቃዊ እስያ እንደዛሬው አጠራር በመካከለኛው ምሥራቅ ነው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በዲዮቅልጥያኖስ ዘመነ መንግሥት ስለ ክርስትና ሃይማኖት ብዙ ተጋድሎ አድርጓል ፤ ወንጌልንም አስተምሮ ያላመነ ሰዎችን ወደ ክርስትና እምነት መልሷል በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በስፋት እንደተገለጸው ቢሩታይት የተባለችውን ልጃገረድ ደራጎን ለተባለው አውሬ ግብር እንድትሆን ቀርባ ሳለች ዘንዶውን በጦር ወግቶ ገድሎ እሷን ከመበላት እንዳዳናት በስፋት ተገልጾዋል፡፡ ከጥንት ጀምሮ እስከ አሁን ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ደራጎኑን ገድሎ ልጃገረዲቱን እንዳዳናት በየቤተ ክርስቲያነ ማለትም በቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕለ አድህኖ ላይ በብዛት ይታያል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰባት ዓመት የተጋድሎ ዘመኑ ሦስት ጊዜ በሰማዕትነት እየሞተ፣ ሦስት ጊዜም በእግዚአብሔር ሃይል እየተነሳ አፅራረ ሃይማኖትን ያሳፈረ ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከመፍረስ ያዳነና የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ከፍ ከፍ የመንፈስ ጀግና ነው፡፡
በተአምራቱም :-
- የደረቁ እንጨቶች እንዲለመልሙ ያደረገ ፤
- በበሬ አምሳል በተሠራ የብረት ቀፎ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ታፍኖ ለመከራያልተበገረ፤
- ሞቶ የነበረ ያንዲት ደኃ ሴትን በሬ በበትሩ ጫፍ አስነስቶ የሰጠ ፤
- አራት መቶ ሠላሳ ዓመት የሆነውን ምውት ያስነሳ፤
- የደረቁና ያረጁ የቤት ምሰሶዎችን እያለመለመ ፍሬ እንዲያፈሩ ያደረገ እውነተኛ ሰማዕት ነው፡፡
ዕውነተኛው ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተወለደበት ለሰማዕትነት እስከ ተጠራበት የኖረውን ሕይወት፤ በሰማዕትነቱ የፈጸመውን ድንቅና ረቂቅ የሆነውን የተጋድሎውን ዜና በዚህ አጭር ጽሑፍ ማቅረብ ፈጽሞ አይቻልም ::
ይሁንና በዘመነ ሰማዕታት፣ በማኅበረ ሰማዕታት ውስጥ ታላቁን ገድል የተጋደለ ለክብር አክሊል የተመረጠ በመሆኑ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍተኛውን የሊቀ ሰማዕትነት ማዕረግ ሰጥቶታል፡፡ ከሰማዕታት መካከል አልቆታል፡፡ ከሴቶች ልጆች ዮሐንስ መጥምቅን የሚበልጠው እንደሌለ በማኅበረ ሰማዕታት መካከልም ቅዱስ ጊርጊስን የሚመስለው የሚተካከለው እንደሌለ መስክሮለታል ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታችን ቀጥሉ ከሐዋርያት ቀድሞ ሰማዕታትነትን በመቀበል ቀዳሜ ሰማዕት እንደተባለ ሁሉ ቅዱስ ጊዮርጊስም በሰማዕታት ማኅበር ውስጥ ቀዳሚ ነው፡፡ ቅድስ ጊዮስጊስ የደረሰበትን ፀዋትወ መከራ ሁሉ በፍጹም እምነት ተቀብሎ በድል በመውጣቱ የልዳ ፀሐይ፣ የፋርስ ኮከብ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ የመጨረሻ ዕረፍቱ ሚያዚያ 23 ቀን ነው፡፡ በሰማዕትነቱ በተቀበለው የምሕረት ቃል ኪዳን ወዳጆቹን ለመርዳትና ለመታደግ ፍጡነ ረድኤት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ሁሉ ከልብ ያፈቅሩታል አማላጅነቱንም ይቀበሉታል በተለይም ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ባለፈውም ሆነ ለአሁነ ለወደፊቱም ቢሆን ባለውለታ ስለሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በስሙ ዝክር እያዘከሩ ፤ ማኅበር እየደገሱ፣ ቤተ ክርስቲያኑን እያነፁና እያሠሩ፣ ለነዳያን ምጽዋት እየሰጡ ይማጸኑታል ፤ ያከብሩታል፡፡
ስለዚህ ይህን ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ከወደቀበት አንስታችሁ በሀሳባችሁ፣ በጉልበታችሁ፣ በገንዘባችሁ፣ በእውቀታችሁ ጀምራችሁ እዚህ በማድረሳችሁ አምላከ ቅዱስ ጊዮርጊስ በረድኤቱ ይጠብቃችሁ፤ የጎደለውን ሁሉ ይሙላላችሁ፤ በረድኤቱ፣ በኃይለ ጸሎቱ ይጠብቃችሁ ይጠብቀን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገ/አማኑኤል
የቤተ ክርስቲያኑ የበላይ ጠባቂ