በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትምህርት ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ሃይማኖት ነው ፥
ቤተክርስቲያኒቱ ያለ ሃይማኖት እግዚአብሔርን ማገልገል እንደማይቻል ታምናለች ።
የእግዚአብሔርም መንግሥት የሚወረሰው በሃይማኖት መሆኑን ለምእመናን ታስተምራለች ።
“ወአልቦ ዘይሜህር እንከ አሐዱ አሐዱ እኅዋሁ ቢጾ ወይብሎ፦
አእምሮ ለእግዚአብሔር ፤ እስመ ኵሎሙ የአምሩኒ ንኡሶሙ ወዓቢዮሙ፡ ይቤ እግዚአብሔር” ። (ት·ኤር ፴፩፡፴፬)
“እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን።
እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር”።
(ት·ኤር 31፡34)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
እምነትና ሥርዓተ አምልኮት
ክፍል ፩: እምት
ምዕራፍ ፩ ሀልዎተ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር መኖር)
እግዚአብሔር የሚለው ስም የባሕርይ ስም ነው ትርጉሙም ዓለምን ፈጥሮ የሚገዛ ማለት ነው ። የማይታይና የማይመረመር ሁሉን ማድረግ የሚችል ሁሉንም የፈጠረ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ዘለዓለማዊ አምላክ መኖሩና ራሱን ለሰው ልጆች እንደገለጠ በቅዱሳት መጻሕፍት ተረጋግጧል ።(ዘጸአ-3፡6)
የዚህን ዘለዓለማዊ አምላክ መኖር ከሚያስረዱን የአእምሮ ማስረጃዎች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው ።
ፍጥረት፦ የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን መኖር ለመረዳት ብዙ ተመራምሮአል። በምርምሩም የእግዚአብሔርን መኖር ወደማወቅ የሚያደርሱ መንገዶችን አግኝቶአል ። ለማንኛውም ነገር ምክንያት አለው ።ለሥዕል ሠዓሊ ፡ ለመጽሐፍ ጸሐፊ ፡ ለወንበር ጠራቢ አለው ። ለሚንቀሳቀስ ነገር ሁሉ እንቀሳቃሽ አለው ። በዚህ መሠረት “ፍጥረት ያለፈጣሪ የተገኘ አይደለም” ወደሚለው እምነት ተደርሶአል ። ፍጥረት ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ፡ አእምሮ ከሌለው ጀምሮ ከፍተኛ አእምሮ እስካለው ድረስ የእግዚአብሔርን መኖር ወደማወቅ ይመራል ፡ስለዚህም ሰሎሞን “እግዚአብሔርን የማወቅ ጉድለት በልባቸው ያለባቸው ሰዎች ሁሉ በእውነት ከንቱ ናቸውና በእነዚህ በሚታዩ ፍጥረቶቹ በዚህ ዓለም የሚኖር እርሱን ያውቁ ዘንድ ተሳናቸው ፡ ሥራውንም እያዩ ፈጣሪያቸውን አላወቁም ፡ …. ፀሐይና ጨረቃን አይተው የፈጠራቸውን ይወቁ‥” (ጥበብ 13፡110) ይላል ። ኢዮብም “እንስሶችን ጠይቅ ያስተምሩህማል ። የሰማይንም ወፎች ጠይቅ ይነግሩህማል ። ወይም ለምድር ተናገር እርስዋም ታስተምርሀለች ፡ የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሀል ፡ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ ፡ ከእነዚህ ሁሉ ይህን የማያውቅ ማን ነው?” ብሏል (ኢዮብ 12፡79) ። ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙር 18፡1-2 “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ የሰማይጠፈርም የእጆቹን ሥራ ያወራል” በማለት ተናግሮአል ።
ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም ከዚህ ግልጥ በሆነ ሁኔታእግዚአብሔር በፍጥረቱ ለፍጥረቱ እንደሚታወቅ ሲያስረዳ እንዲህይላል። “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በሥነ ፍጥረት ይታወቃል ።” (ሮሜ 1፡19–20)።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን የሐዋርያውን መልእክት በተረጐመበት ድርሳኑ እንዲህ ይላል “እግዚአብሔር ገናናነቱ በሥራው ይታወቅ ዘንድ ሁሉን ካለመኖር ወደ መኖር አመጣ ። ነፍስ በሰው ውስጥ አንደማትታይ ግን በሰውነት እንቅስቃሴ እንደምትታወቅ እግዚአብሔርም በሥጋዊ ዐይን አይታይም ግን በፈቃዱና በሥራው ይገለጣል ፡ ይታወቃልም ። በባሕር ላይ ተንሳፍፋ ወደፊት የምትጓዝ መርከብን የሚመለከት ሰው በውስጥዋ የሚመራት ነጂ እንዳለ ማወቅ አለበት እንደዚሁም ምንም በዓይነ ሥጋ ባይታይ ሁሉንም የሚመራ እግዚአብሔር እንደሆነ ማስተዋል ይገባዋል ። (የዮሐንስ አፈወርቅ ትርጓሜ ፡ሮሜ 1፡19-20) ።
ልቡና ፦ “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና እነርሱም ልቡናቸው ሲመሰክርላቸው አሳባቸውም እርስ በርሱ ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።” (ሮሜ 2፡14-15)። ሰው በልቡናው ውስጥ ባለው መንፈሳዊ ሕግ አነሳሽነት መልካም ይሠራል ከክፉም ይርቃል። ተላልፎ ክፉ ቢሠራም እንኳ ሕሊናው ይወቅሰዋል ። መልካም የሚሠራ ዋጋ እንደሚያገኝ ክፉ የሚሠራም እንደሚቀጣ ይኸው ሕሊናው ይመሰክርበታል ። ይህ ዓይነቱ ሕሊና ለደግም ሆነ ለክፉ እንደሥራው ዋጋ የሚከፍል አንድ አምላክ መኖሩን ወደ ማወቅ ይመራል ።
ታሪክ፦ በዚህ ዓለም አምልኮት የሌለው ሕዝብ እንዳልኖረ የሰውልጅ ታሪክ ያስረዳል ። ከጥንት ጀምሮ እስከ አለንበት ዘመን ድረስ የአልምኮቱ ዓይነት ይለያይ እንጂ ሁሉም በየወገኑ ባዕድ አምላክ ወይም ብዙዎች አማልክትን ያመልካል ። ይህም ሁሉ የሚያሳየው የአንድ እውነተኛ አምላክ መኖርን ነው ። እግዚአብሔር ባይኖር ሰው ይህን የአምልኮት ጠባይ ከየት ሊያገኝ ቻለ? (የሐዋ.14፡11–16 ፡ 17፡26–29) ።
በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እግዚአብሔር መኖር በሰፊው ከመነገሩም በላይ ስለ እርሱ የተሰጡ መግለጫዎች አሉ ። እነርሱም የሚከተሉትናቸው ።
ቅድስና፦ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው ከክፉ ወይም ከርኩስ ነገር ጋርምንም ግንኙነት የለውም ። እርሱ ራሱ “እኔ ቅዱስ እንደሆንሁ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ሲል ተናግሮአል ። (ዘሌዋ 19፡2 ። 1ጴጥ-1፡16)። ሁልጊዜ በመላእክት ቅዱስ ፡ ቅዱስ ፡ ቅዱስ ፡ እየተባለ ሲመሰገን ይኖራል(ኢሳ.6፡3) ።
ፍቅር፡- እግዚአብሔር ፍቅር በመሆኑ ፍጥረቱን ይወዳል መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ለፍጥረቱ ይሰጣል ።እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑ በወንጌላዊው ዮሐንስ ወንጌልና መልእክታት ተደጋግሞ ተገልጦአል ። (1 ዮሐ 4፡8) በኋላም ሰው መሆኑ ፍቅሩንያመለክታል ። (ዮሐ.3፡16 ። ሮሜ 5፡5)።
ጽድቅ፡- እግዚአብሔር በሁሉ እውነተኛ ነው ፡ በእውነተኛነቱ ለሁሉ በትክክል ይፈርዳል ፡ (1 ሳሙ 2፡2 ። 2 ጢሞ 4፡ 8) ዮሐንስ በራእዩ16፡7 “አዎ ጌታዬ ሁሉን የምትገዛ ፍርድህ እውነተኛና የሚገባ ነው”ይላል ።
ጥበብ፡- ፍጥረትንና የፍጥረቱን ሥነ ሥርዓት ክንውን ስንመለከት የእግዚአብሔርን ፍጹም ጥበብ እንረዳለን። ነቢዩ ዳዊት እግዚአብሔር በጥበብ የሠራውን ሁሉ በማድነቅ እንዲህ ይላል ። “አቤቱ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው ሁሉን በጥበብ አደረግህ” (መዝ፤ 103፡24)።
ከአንድ እስከ አራት ከተመለከትናቸው የባሕርዩ መግለጫዎችየተለዩ ሌሎች የግዚአብሔር የባሕርዩ መግለጫዎች አሉ ።
ሁሉን ቻይነት፡-
(ከሃሌ ኩሎ) ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር ፈጽሞ የለም ፤ ሁሉን ማድረግ ይችላል ፡ እግዚአብሔር ራሱ ለአብርሃም “ሁሉን ቻይ ነኝ” ብሎ ገልጦለታል ። (ዘፍ 17፡1። 18፡14 ። ሉቃ 1፡37)
ሁሉን ማወቅ፡-
እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ከመሆኑ በፊት ያውቀዋል። ነገሮችን ሁሉ ከመታሰባቸውና ከመሠራታቸው በፊትያውቃቸዋል ። (መዝ 138፡2፡ ዮሐ 2፡25) ።
ምሉዕነት፡-
እግዚአብሔር በቦታና በጊዜ አይወሰንም በየትም ቦታ አለ ፡ ምንም እንኳን ስለ ልዕልናው በሰማይ እንደሚኖር ቢነገርም በሰማይ ብቻ አይወሰንም ። ቅዱስ ዳዊት እንዲህ ይላል “ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ አለህ ወደ ሲኦልም ብወርድ በዚያ አለህ ” (መዝ 138፡7–10 ። ኤር 23፡23 ሠለስቱ ምእት ቅዳሴ)
ዘለዓለማዊነት፡-
እግዚአብሔር በዘመናት አይወሰንም ፡ ከዘመንበፊት ነበረ ፡ ዘመናትንም አሳልፎ ይኖራል ። (መዝ 89፡12) በጠቅላላ አነጋገር እግዚአብሔር መጀመሪያና መጨረሻ የለውም ራሱ መጀመሪያናመጨረሻ ነው በእርሱ ዘንድ ለውጥ የለም ። (ኢሳ 44፡6 ። ያዕ 1፡17)
ምዕራፍ ፪ ሥነ ፍጥረት
ቅዱስ መጽሐፍ የእግዚአብሔርን መኖር በማረጋገጥ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ በማለት ይጀምራል ። (ዘፍ 1፡1) ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ 3፡4 ላይ “ሁሉን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው” ይላል ።
እግዚአብሔር ሁሉን አስገኘ ፡ ለሁሉ ነገር መገኛ ጥንትና መሠረት ነው ። ለእርሱ ግን ለህላዌው ምክንያት የለውም ። (የሐዋርያት ጸሎተሃይማኖት) እግዚአብሔር ይህን የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም በውስጣቸውም ያሉትን ሁሉ ከቸርነቱ ብዛት የተነሣ ፈጠረ ።(ኢሳ.42፡5) ።
እግዚአብሔር ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር ያስገኘው “ለይኩን” ባለው ቃሉ ብቻ ነው ። ይህ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ምንም ነገር አልነበረምና (ጥበበ ሰሎሞን 11፡17 ። 1 መቃብ 27፡1 ቅዱስ ጳውሎስም “ዓለሞች ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠሩ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን” (ዕብ11፡3 ) በማለት እግዚአብሔር ፍጥረትን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶመፍጠሩን አስረድቷል ።
ፈጣሬ ፍጥረታት እግዚኣብሔር ሥነ ፍጥረትን በየመልኩና በየወገኑ መፍጠሩ ክብሩ ይገለጥበትና ስሙ ይቀደስበት ዘንድ ነው ።ይህንም ነቢዩ ኢሳይያስ “ፍጥረታትን ሁሉ ለክብሬ ፈጠርኋቸው አለ እግዚአብሔር” ብሎ ተናግሮአል ። (ኢሳ 43፡7)
ፍጥረታት ሁሉ በየወገናቸው ከዕለተ እሑድ እስከ ዕለተ ዓርብ ባሉት ስድስት ቀናት በቅደም ተከተል መፈጠራቸውን ቅዱስ መጽሐፍ ይናገራል ።
እነዚህም በስድስቱ ዕለታት የተፈጠሩ ፍጥረታት በየወገን በየወገናቸው ተቆጥረው ሃያ ሁለት መሆናቸውን መጽሐፈ ኩፋሌ ይናገራል ። (ዘፍ 1፡1-31) ኩፋሌ ፡ 3 9) በየዕለቱ የተፈጠሩት ፍጥረታትም በሚከተለው ሁኔታ የተገለጡት ናቸው ።
ሀ) የእሑድ ፍጥረታት
- እሳት
- ነፋስ
- ውሃ
- መሬት (ዐራቱ ባሕርያት)
- ጨለማ
- ሰባቱ ሰማያት
- መላእክት
- ብርሃን ናቸው (ኩፋሌ 2፡58 ዘፍ 1፡15) ።
ለ) የሰኞ ፍጥረት
በምድር ላይ ሞልቶ የነበረው ውሃ ተከፍሎ ጠፈር ተገለጠ (ዘፍ 1፡6 8 ። ኩፋሌ 2፡9 ። ዘፍ 1 ፡9)
ሐ) የማክሰኞ ፍጥረት
- በጣት የሚለቀሙ አትክልት
- በማጭድ የሚታጨዱ አዝርዕት
- በምሣር የሚቆረጡ ዕፀዋት ናቸው ። (ዘፍ 1፡11–13 ።)
መ) የረቡዕ ፍጥረታት
- ፀሐይ
- ጨረቃ
- ከዋክብት ናቸው (ዘፍ 1-14–16)
ሠ) የሐሙስ ፍጥረታት
በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀሱ ከባሕር ውስጥ ፡
- በደረት የሚሳቡ
- በእግር የሚያኮበኩቡ
- በክንፍ የሚበሩ እንስሳት አራዊትና አዕዋፍ ናቸው ፡ (ዘፍ 1፡20–22)።
ረ) የዐርብ ፍጥረታት
በደመ ነፍስ ሕይወት የሚንቀሳቀሱ በየብስ የሚኖሩ፡
- ዘመደ እንስሳ ፡
- ዘመደ አዕዋፍ ፡
- ዘመደ አራዊት ፡
- በነባቢት ነፍስ የሚንቀሳቀስ ሰው ናቸው (ዘፍ 1፡2428)።
እነዚህን ሁሉ ፍጥረታት በየወገኑ ከፈጠራቸው በኋላ መልካም እንደሆኑ አይቶ እግዚአብሔር በሥራው ደስ አለው እንዲበዙ ምባረካቸው። (ዘፍ 1፡21 ። መዝ 103፡31)።
ምዕራፍ ፫ አምስቱ አዕማደ ምሥጢር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሠረተ እምነትዋን የምትገልጥባቸውና የምታስተምርባቸው አምስት አዕማደ ምሥጢር አሏት ። አዕማድ ማለትም ምሰሶዎች ማለት ነው ። የምሥጢር ምሰሶዎችም የተባሉበት ምክንያት ቤት በምሰሶ ተደግፎ እንደሚጸና ምእመናንን በትምህርተ ሃይማኖት ደግፈው የሚያጸኑ ስለሆነ ነው። እነዚህም አምስቱ አዕማደ ምሥጢር መጽሐፋዊ መሠረት ያላቸው ናቸው (1 ቆሮ.14፡19።) በዚህም መሠረት አምስቱ አዕማደ ምሥጢር የእምነታችን መግለጫ በሆነው በጸሎተ ሃይማኖት ተዘርዝረው ይተረጐማሉ ።
ይህ ክፍል የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት የሚገለጥበት የምሥጢር ዓምድ ነው ። ሥላሴ በስም በግብር ፣ በአካል ሦስት ሲሆኑ በባሕርይ ፣በመለኮት ፡ በህልውና በፈቃድ አንድ ናቸው ።
የስም ሦስትነት፡ አብ ፡ ወልድ ፡ መንፈስ ቅዱስ ፣
የግብር ሦስትነት፡ አብ ወላዲ ፡ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ ነው ።
የአካል ሦስትነት፡ ለአብ ፍጹም አካል አለው ፣ ለወልድ ፍጹም አካል አለው ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል አለው።
እብ ልብ ነው፡ ወልድ ቃል ነው፤ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ነው ።
አብ ለራሱ ለባዊ ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው ። ወልድ ለራሱ ቃል ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው ። መንፈስ ቅዱስ ለራሱ እስትንፋስ (ሕይወት) ሆኖ ለአብና ለወልድ እስትንፋስ (ሕይወት) ነው ።
ሥላሴ በስም ፣ በግብር ፣ በአካል ሦስት ናቸው ብንልም በባሕርይ በመለኮት በህልውና በፈቃድ አንድ ስለሆኑ አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይባሉም። አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ፣ በየአካላቸው ሲኖሩህልውናቸው አንዲት ናት ። (አቡ ሊዲስ ሃይ‧አ/ምዕ 40 ክፍ 4 ቁ 6)
የሥላሴ የሦስትነት ስማቸው የአንዱ ወደ አንዱ አይፋለስም። ይህም ማለት የአብ ስም ተለውጦ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ፣ የወልድ ስም ተለውጦ አብ መንፈስ ቅዱስ ፤ የመንፈስ ቅዱስ ስም ተለውጦ አብ ወልድ ተብሎ አይጠራም ። አብ ፡ አብ ነው ። ወልድ ወልድ ነው ፡ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ነው ። ሦስቱም በየስማቸውና በየአካላቸው ጸንተው ይኖራሉ (አግናጢዎስ ሰማዕት ሃይ አበ) ምዕ 11 ክፍ 1 ቁ 78።)
በአንድነት ስማቸው ግን – እግዚአብሔር ፡ አምላክ በመባል ሦስቱም ይጠሩበታል ። እግዚአብሔር አብ ፡ እግዚአብሔር ወልድ ፡እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድ እግዚአብሔር ፡ አብ ፡ አምላክ ወልድ አምላክ ፡ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ፡ አንድ አምላክ ፡ ይባላል ። ይህንም ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት በሃይማኖት አበው ሲያስረዱ “በእግዚአብሔር አብ ፡ በእግዚአብሔር ወልድ ፡ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እናምናለን” ብለዋል (ሃይ·አበ ዘሠለስቱ ምእት/ምዕ19 ፡ ክፍል 1 ቁጥር 30።)
የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ሐዋርያዊ አትናቴዎስም «አብ አምላክ ነው ፡ ወልድ አምላክ ነው ፣ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው ፡ ግን አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይባሉም» በማለት ገልጾአል (ሐዋርያዊ አትናቴዎስ ሃይ·አበ ። ምዕ 24 ክፍል 4 ቁጥር 4)
ስለ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በብሉይና በሐዲስ ኪዳናት በብዙ ቦታ ተገልጾአል ።
በብሉይ ኪዳን
ዘፍ 1፡26። 2፡18። 3፡22። 11፡7። 18፡13። መዝ‧33፡6። 146፡5። ኢሳ 6፡3-8።
በሐዲስ ኪዳን
ማቴ 3፡16-17። 28፡19። ዮሐ 14፡26። 2 ቆሮ 14፡13። 1 ጴጥ 1፡2። 1 ዮሐ 5፡7–8።
ምሥጢረ ሥጋዌ ከሦስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ፣ ከነፍስዋም ነፍስ ነሥቶ በሥጋ የመገለጹ ፡ አምላክ ሰው ፣ ሰው አምላክ ፣ የመሆኑ ምሥጢር ነው ። «ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ” (ዮሐ 1፡14)።
እግዚአብሔር ወልድ ሰው የሆነበት ምክንያት
እግዚአብሔር የመጀመሪያዎቹን ሰዎች አዳምንና ሔዋንን በንጹሕ ባሕርይ ያለሞት ፈጥሮአቸዋል ። “እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና”።(መጽ ጥበብ 1፡13)።
ይሁን እንጂ የሰው ልጅ የተሰጠውን ትእዛዝ በማፍረስ ስለበደለ ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ ፡ ርደተ መቃብርና ርደተ ገሃነም ተፈረደበት (ዘፍ3፡19-24) እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና ነዋሪ ይሆን ዘንድ ፍጥረትን ፈጥሮዋል እንጂ የሰዎች ጥፋት ደስ አያሰኘውም ፣ በእጃችሁ ሥራ ሞትን አታምጡ ። የሰውም መፈጠር ፡ ለደኅንነት ነውና ። በእነርሱ ዘንድ ሁሉን የሚያጠፋ የሞት መርዝ ኃጢአት አልነበረምና ። ሕይወት የማታልፍ ስለሆነች ለመቃብርም በዚህ ዓለም ግዛት አልነበረውምና እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎች ግን በቃል ጠሩት ። ባልንጀራም አደረጉት በዚሁም ጠፉ (ጥበብ 1፡13-17። ሮሜ 6፡23። “እግዚአብሔር ለሞት አልሠራንምናለሕይወት እንጂ” 1 ተሰ 5፡9)።
አዳምና ሔዋን በበደላቸው ከክብራቸው ተዋረዱ ፡ ከጸጋቸው ተራቆቱ ፡ ከተድላ ገነት ወጡ ፡ ተባረሩ ፡ በሥራቸው በራሳቸው ላይ ብዙመከራን አመጡ ። ተጨነቁ ፣ ተቸገሩ ፤ ለአጋንንትም ተገዦች ሆኑ ። በኃጢአት ምክንያት ወደ ዓለም የገባው ሞት በሰው ላይ ሠለጠነ ፡ ከአዳም እስከ ክርስቶስ የነበሩትን ሁሉ ሞት አንድ አድርጎ ገዛቸው ። (ሮሜ 5፡12-14) ይህ ሁሉ መከራ የመጣባቸው ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፋቸው መሆኑን አውቀው ተጸጸቱ ፡ አዘኑ ፣ አለቀሱ ፣ ንስሐ ገብተው ፣ፈጣሪያቸውን ለመኑት ። እግዚአብሔርም በፈታሒነቱ አንጻር መሐሪነቱ አለና የአዳምንና የሔዋንን ንስሐቸውን ተቀብሎ ኀዘናቸውንና ለቅሶአቸውን ተመልክቶ ሊያድናቸው ወደደ ፡ ተስፋም ሰጣቸው ፡ (ኢሳ 63፡8 ። ዕብ 2፡14-16።)
ይህም የተሰጠው ተስፋ የሚፈጸምበት ዘመን በደረሰ ጊዜ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲያገኝ ፣ ልዑል እግዚአብሔር ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን አንድ የባሕርይ ልጁን ወደ ዓለም ላከው ፡እግዚአብሔር ወልድም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ንጽሕት ከምትሆን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖ ተወለደ ። ሰው ሆነ ማለትም በተለየ አካሉ ነፍስና ሥጋን ተዋሐደ ማለት ነው። በዚህም የነቢያት ቃል ሁሉ ተፈጸመ (ኢሳ 7፡14፡ 9፡6፡ ሚክ 5፡2፡ ገላ 4፡4)።
መለኮት ከሥጋ ፡ ሥጋ ከመለኮት ጋር ያለ መለወጥ ፡ ያለመቀላቀል ፡ ያለ መለያየትና ያለ መከፈል በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ ። ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ ፡ ሰውም ከሆነ በኋላ አንድ ወልድ ፣ አንድ ክርስቶስ ነው። (ቄርሎስ ሃይ‧አበ‧ምዕ – 78 ክፍ 48 ቁ 9–18)። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙም ፡ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ፤ አምላክም የሆነ ሰው እርሱ ብቻ ነው» ብሎአል ሃ አ ምዕ 61 ክፍል4 ቁጥር 23-ሥጋም በተዋሕዶተ ቃል እንደከበረ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሥጋ የነበረ ንዴት በተዋሕዶተ ቃል ጠፋ ፡ የቃል ክብር ለሥጋ በተዋሕዶ ገንዘቡ ሆነ» ብሎአል ። (ዮሐ ኣፈ ሃይ አ ምዕ- 66 ክፍ 9 ቁጥ 1819)። ከተወለደም በኋላ ከኃጢአት በቀር ሰው የሚሠራውን ሥራ ሁሉ እየሠራ አደገ ፣ በዚህም ዓለም 33 ዓመት ከሦስት ወር ኑሮና አስተምሮ ስለእኛ የሞት ፍርድን ተቀበለ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ ፡ በሞቱም ሞትን አጠፋ ፡ ዓለምን አዳነ ፡ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ተነሣ ። ከተነሣም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ እየታየ ጉባኤ ሠርቶም መጽሐፈ ኪዳንን እያስተማረ በምድር ላይ አርባ ቀን ቆየ ። በአርባኛውም ቀን ደቀ መዛሙርቱ እያዩት በመላእክት ምስጋናና በክብር ወደ ሰማይዐረገ ። በአባቱም ቀኝ (ዕሪና) ተቀመጠ ፤ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታንላይ ሊፈርድና ለሁሉም እንደሥራው ዋጋውን ይከፍል ዘንድ ይመጣል ። (ዮሐ3፡13። 1ጴጥ 3፡22። ማቴ 25፡31። ኤፌ 4፡8-10። የሐዋ 2፡30። 2ቆሮ 5፡14 ።)
ስለዚህ በምሥጢረ ሥጋዌ የሚገለጠው ትምህርት ክርስቶስን ቃለአብ ወመንፈስ ቅዱስ ፡ ድንግል ማርያምን በአማን ወላዲተ አምላክ ወላዲተ ቃል ፣ ብሎ ማመን ነው። ቄርሎስ ሃይ/አ።
ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ ለሚያምን ሰውሁሉ የሚሰጥ የኃጢአት መደምሰሻ ፡ ከእግዚአብሔር የልጅነትን ጸጋ መቀበያ ፣ የመንግሥተ ሰማያትም መውረሻ ነው ። ምሥጢር መባሉም ካህኑ ለጥምቀት የተመደበውን ጸሎት አድርሶ ሲባርከው ውሃው ተለውጦ ማየ ገቦ ስለሚሆንና ከእግዚአብሔር ዘንድ የጸጋ ልጅነትን ስለሚያሰጥነው ። (ዮሐ 19፡34-35)።
አምኖ የሚጠመቅ ሁሉ የኃጢአት ሥርየትን ያገኛል ፤ « ወነኦምንበአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት ፡- ኃጢአትን ለማስተሥረይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን » (ጸሎተ ሃይማኖት)
ማንም ሰው በጥምቀት ከእግዚአብሔር ይወለዳል ፣ ከፍዳ ይድናል ። “ያመነ የተጠመቀም ይድናል ፣ ያላመነና ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል” (ማር 16፡16 ፤ የሐዋ 2፡28)። ከሥላሴ መወለድም የእግዚአብሔርን ርስት መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ነው ። መንግሥተ ሰማያትም በጥምቀት እንጂ ያለ ጥምቀት ልንገባባት እንደማንችል ጌታችን አስተምሮአል ። «እውነት እውነት እልሀለሁ ማንም ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይችልም» (ዮሐ- 3፡5። ቲቶ 3፡47)።
ስለ ጥምቀት በሕግና በነቢያት የተነገሩ ትንቢቶችና የተገለጡ ምሳሌዎች አሉ ።
ሀ) ትንቢት፦ «የጠራ ውሃ እረጫችሁአለሁ ትጠሩማላችሁ» ከርኵሰታችሁም ከጣኦቶቻችሁም ሁሉ አነጻችሁአለሁ። (ሕዝ· 36፡25 ። ሚክ 7፡19) ።
ለ) ምሳሌ፦
1 ግዝረት
ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ በብሉይ ኪዳን ሲሠራበት ኖሮአል ። ግዝረት ለአብርሃም የቃል ኪዳን ምልክት ሆኖ በመሰጠቱ በስምንተኛው ቀን ያልተገረዘ ሁሉ ከአብርሃም ቤተሰብ አይቈጠርም ምድረር ስትንም አይወርስም ፡ ከተስፋው አይካፈልም ። የእግዚአብሔርምወገን አይባልም ነበር ። (ዘፍ 17፡7)።
በሐዲስ ኪዳን በግዝረት ፈንታ ጥምቀት ተተክቶአል ። ያልተጠመቀሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ አይባልም ፡ መንግሥተ ሰማያትን አይወርስም ። (ቆላስይስ 2፡11)
በብሉይ ኪዳን መፈጸሚያ ፣ በሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ የነበረው መጥምቁ ዮሐንስም በውሃ ያጠምቅ ነበር ። (ማር. 1፡48)
2 የኖኅ መርከብና የእስራኤል ቀይ ባሕርን መሻገር የጥምቀት ምሳሌዎች ነበሩ ፡ (1ኛ ጴጥ 3፡19 ፡ 1 ቆሮ 10፡2)።ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢቱን ለመፈጸም ፣ ምሳሌውን አማናዊ ለማድረግ በማየ ዮርዳኖስ (ወንዝ) በዮሐንስ እጅ ተጠምቆአል ። (ማቴ 3፡16። ማር 19። ሉቃ 3፡21 ። ዮሐ 1፡31)።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምሥጢረ ጥምቀትን ለወንዶች በ40 ቀን ፣ ለሴቶች በ80 ቀን ትፈጽማለች ። ይህም ዕድሜ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ከእግዚአብሔር ልጅነትን የተቀበሉበትነው ። (ኩፋሌ 4፡2–15)።
ቁርባን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ፣ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የምንሆንበት ምሥጢር ነው ። «እውነት እውነት እላችኋለሁ የወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስን ሥጋውን ካልበላችሁ ደሙን ካልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም ። ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው ። ሥጋዬና ደሜ ሕይወትነት ያለው እውነተኛ ምግብ ነውና ። ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ ከእኔ ጋር ይኖራል ። እኔም ከእርሱ ጋር እኖራለሁ» (ዮሐ 6፡53 57)። ተብሎ ተጽፎአልና ።
ስለ ምሥጢረ ቁርባን አስቀድሞ የተነገሩ ትንቢቶችና የተገለጡ ምሳሌዎች አሉ ።
ትንቢት
«ከስንዴ ፍሬና ከወይን ፡ ከዘይትም ይልቅ በዛ»(መዝ 4፡7)። ጥበብ ቤትዋን ሠራች ፣ ሰባቱንም ምሰሶዎችዋን አቆመች ፣ ፍሪዳዋን አረደች ፣ የወይን ጠጅዋንም ደባለቀች ፣ ማዕዷንም አዘጋጀች (ምሳሌ 9፡19)።
የሰው የሕይወቱ መጀመሪያ እህልና ውሃ ወይንና ስንዴ ነው።(ሲራ 39:26)
እነዚህም ትንቢቶች በመስቀል ላይ የተሠዋው በግዐ ፋሲካ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውን ደሙን በስንዴ ኅብስትና በወይን እንደሚሰጥ የተነገሩናቸው ።
ምሳሌ
የእስራኤል ልጆች ከግብጽ የባርነት አገዛዝ በወጡበት ጊዜ አርደው ሥጋውን እንዲበሉት ደሙንም የቤታቸውን መቃን ጉበንና መድረኩን ረጭተው ከመቅሠፍትና ከሞተ በኵር እንዲድኑ የተሰጠው የፋሲካቸው በግ በመስቀል ላይ የተሠዋውና ሥጋውንና ደሙን ለሰው ልጆች ሕይወት ቤዛ አድርጎ የሰጠው የወልደ እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው ። ይህም «እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» (ዮሐ 1፡29) ተብሎ በተጻፈው ታውቋል ።
ለወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ የሆነው ካህን መልከ ጼዴቅም በኅብስትና በወይን ያስታኩት ነበር ። (ዘፍ 14፡18)።
እነዚህን ትንቢቶችና ምሳሌዎች ለመፈጸምና አማናዊ ለማድረግ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሴተ ሐሙስ በተዘጋጀው የፋሲካ ዕራት ኅብስቱን አንስቶ አመስግኖ ባርኮ ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ «ይህ ሥጋዬ ነው ፣ እንኩ ብሉ» ብሎ ሰጣቸው ጽዋውንም አንሥቶ አመስግኖ ባርኮ «እንኩ ሁላችሁ ከዚህ ጠጡ ፣ ለሐዲስ ኪዳን ኃጢአትን ለማስተሠረይ ስለ ብዙ ሰዎች የሚፈስ ደሜ ይህ ነው» ብሎ ሰጣቸው(ማቴ 26፡28። ማር 14፡22። ሉቃ 22፡19)። ይህ ምሥጢር አሁንም በቤተክርስቲያናችን ይፈጸማል ።
ቄሱ በቅዳሴ ጊዜ ኅብስቱን በፃሕል ወይኑን በጽዋዕ አድርጎ እየባረከጸሎተ ቅዳሴውን ሲያደርስበት ኅብስቱ ተለውጦ አማናዊ ሥጋ ወልደእግዚአብሔር ፣ ወይኑ ተለውጦ አማናዊ ደመ ወልደ እግዚኣብሔር ይሆናል ።
ይህንም ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ «ካህኑ፦ ሳይባርከውና ሳያከብረው ኅብስትና ወይን እንደሆነ ካህኑ በባረከውና ባከበረው ጊዜ ግን ኅብስቱ ከኅብስትነት የአምላክ ሥጋ ወደ መሆን ፣ ወይኑም ከወይንነት ወልደ እግዚአብሔር ደም ወደ መሆን እንደሚለወጥ እናምናለን» ብሎአል ። (አትናቴዎስ ሃይ/አበው ምዕ 28 ክፍ 14 ቁ 22 )
ስለዚህ በምሴተ ኀሙስ ሐዋርያት የተቀበሉት በዕለተ ዐርብ በመስቀል ላይ የተሠዋው ፣ ዛሬም በአራቱ መዓዝነ ዓለም እስከ ምጽአት ድረስ የሚሠዋው መሥዋዕት አንድ ነው ። ይኸውም «አማናዊ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔር ፡ አማናዊ ደመ ወልደ እግዚአብሔር ነው እንጂ ምሳሌ ወይም መታሰቢያ አይደለም» ብላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታምናለች ታሳምናለች ። « ዛሬ በየጊዜው ካህናት የሚያቀርቡአት ንጽሕት መሥዋዕት ያን ጊዜ በቀራንዮ በመልዕልተ መስቀል የተሠዋችው ናት ። (ዮሐ እፈ ቅዳሴ፡8)።
ትንሣኤ ሙታን ማለት ከአዳም እስከ ምጽአተ ክርስቶስ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩና የሚለዩ የሰው ልጆች ሁሉ በነፍስና በሥጋ አዲስ ሕይወት ለብሰው የሚነሡበት ምሥጢር ነው ።
ሰው ሁሉ በሚሞትበት ጊዜ የጻድቅም ሆነ የኃጥእ ሥጋውበመቃብር ይቆያል ። የጻድቃን ነፍስ በገነት ፣ የኀጥአን ነፍስ በሲኦልትቆያለች ። (ሉቃ 16፡19–31)።
የዚህ ዓለም ፍጻሜ ሲደርስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕያዋንናበሙታን ሊፈርድ በሚመጣበት ጊዜ የሰው ልጆች ሁሉ ይነሣሉ ።«ስለዚህ ነገር አታድንቁ በመቃብር ያሉት ሙታን ሁሉ ቃሉን የሚሰሙባት ሰዓት ትመጣለች ሕጉን የፈጸሙ በሕይወት ለመኖር ይነሣሉ ።ክፉ ሥራን የሠሩት ግን በፍዳና በጨለማ ለመኖር ይነሣሉ» ። (ዮሐ· 5:28)
ስለ ትንሣኤ ሙታን እምነትና ትምህርት ማረጋገጫ በብሉያት በሐዲሳት በብዙ ቦታ ይገኛል ። በዘዳግም 32፡39 ላይ «እኔ እገድላለሁ ፣አድንማለሁ» በማለት ራሱ እግዚአብሔር የተናረው ቃል ተስፋ ትንሣኤን የሚያረጋግጥ ነው ። ነቢዩ ኢሳይያስ «ሙታን ይነሣሉ ፣በመቃብር ያሉ ሕያዋን ይሆናሉ ። በምድር ውስጥ ያሉም ደስ ይላቸዋል ።ከአንተ የሚገኝ ጠል ሕይወታቸው ነውና» ። (ኢሳ 26፡19-20)። ዳንኤልም «በዚያም በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል። በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎቹ ይነቃሉ ፡እኩሌቶቹ ወደ ዘለዓለም ሕይወት ፣ እኩሌቶቹም ወደ ዕፍረትና ወደዘለዓለም ጉስቁልና ይሄዳሉ» በማለት ተናግሮአል ። (ዳን 12፡13)።
« እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደሆነ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ ። እኔ ራሴ አየዋለሁ ዓይኖቼም ይመለከቱታል» ሲል ፡ ኢዮብ የትንሣኤን ነገር ገልጦአል ። (ኢዮብ 19:25-27)
የትንሣኤ ሙታን ትምህርት በቃል ብቻ የተነገረ አይደለም ከሞቱ ሰዎች መካከል እየተነሡ በተግባር ተገልጦአል ነቢዩ ኤልያስና ደቀመዝሙሩ ኤልሳዕ ሙታንን አስነሥተዋል ። (1 ነገሥ 17፡21 ። 2 ነገሥ 13፡21)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚህ ዓለም በሚያስተምርበት ጊዜ ሙታንን አስነሥቶአል ። (ማቴ 9፡25። ሉቃ 7፡15። ዮሐ 11-14)።እንደዚሁም ሐዋርያት በትምህርት ጊዜያቸው ሙታንን አስነሥተዋል ። ጌታችን በተሰቀለበትም ዕለት ከእግረ መስቀሉ ብዙዎች ሙታን ተነሥተዋል ። (ማቴ 27፡52)።
ይህ ሁሉ የሚያመለክተው የሰው ልጅ በመቃብር ውስጥ ፈርሶና በስብሶ እንደ ማይቀርና በመጨረሻ ቀን እንደሚነሣ ነው። ለትንሣኤያችን መሠረት የምናደርገው ግን የክርስቶስን ትንሣኤ ነው። «ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ እኛንም በሐዲስ ትንሣኤ እንደሚያስነሣን እናውቃለን» ፣ (2 ቆሮ 4፡14)። የቤተክርስቲያን ሊቃውንት አሞንዮስና አውሳብዮስም « ክርስቶስ የሥጋችንን መነሣት ያስረዳን ዘንድ ተነሣ» ብለዋል (መቅድመ ወንጌል)
ትንሣኤ ለሰው ዘር ሁሉ ነው ፣ ጻድቃንም ኃጥአንም ይነሣሉ ።የመጨረሻው የሙታን ትንሣኤ የሚሆነውም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማሳለፍ በሚመጣበት ጊዜ ነው ።
በዘመኑ መጨረሻ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስበሙታንና በሕያዋን ይፈርድ ዘንድ በክብሩና በጌትነቱ ይመጣል ። (መዝ49፡2 ማቴ 25፡31–32። ራእ 1፥7)። አስቀድሞም መላእክትን ይልካቸዋል። እነርሱም የመለከት ድምፅ ያሰማሉ ፣ ሙታንም ይነሣሉ ፣ ምድርም አደራዋን ታስረክባለች ።
ከዚህ በኋላ ጻድቃንን በቀኙ ፣ ኃጥአንን በግራው ያቆማቸዋል ፣ ያንጊዜ ጻድቃን በበጎ ምግባራቸው ይመሰገናሉ ፣ ኃጥአንም በክፉ ምግባራቸው ይወቀሳሉ ። ጻድቃን ከፀሐይ ሰባት እጅ አብርተው አምላካቸው ክርስቶስን መስለው መንግሥቱን ይወርሳሉ። ኃጥአን ግን ጠቁረው ፣ ጨለማ ለብሰው ለሰይጣንና ለሠራዊቱ ወደ ተዘጋጀው ወደ ዘለዓለምኲነኔ ይሄዳሉ። (ማቴ 13፡42–49። ማቴ 25፡31-43። 2 ቆሮ 5፡10። ራእ 20፡12)።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖትን ለምእመናን የምታስተምረው ከዚህ በላይ በአምስት ተከፍለውበተገለጡት አዕማደ ምሥጢር መሠረትነት ነው።
ምዕራፍ ፬ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲየናት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰባት ዐበይትምሥጢራት ምእመናንን ታገለግላለች ምሥጢራት የተባሉበትምምክንያት በዓይናችን ልናያቸው በእጃችን ልንዳስሳቸው የማንችል ልዩልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በእነዚሁ ምሥጢራት አማካይነት የሚሰጡን ስለሆነ ነው ።
ሰባቱ ምሥጢራት
1ኛ· ጥምቀት
2ኛ· ቅብዓተ ሜሮን
3ኛ· ቁርባን
4ኛ· ክህነት
5ኛ· ተክሊል
6ኛ· ንስሐ
7ኛ· ቀንዲል ናቸው ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአዕማድ ምሳሌነት በምሳሌ ሰሎሞን የተነገረውን መነሻ በማድረግ ምሥጢራት ሰባት መሆናቸውን ትቀበላለች ፣ ምሳሌ ሰሎሞን 9፡1 ፣ እነዚህ ሰባት ምሥጢራት በሚታየውና በሚዳሰሰው በግዙፉ አካል አማካይነት ረቂቁን የማይታየውንና የማይዳሰሰውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ለምእመናን የምታሳትፍባቸው ናቸው ። ከእነዚህ ሰባተ ምሥጢራት ስድስቱ በጳጳስም ፥ በቄስም ይፈጸማሉ ፣ የክህነትን ሥልጣን መስጠት ግን የሚፈጸመው በጳጳስ ብቻ ነው።
ጥምቀት፣ ከሰባቱ ምሥጢራት የመጀመሪያው ጥምቀት ነው፣ጥምቀት ዳግመኛ ተወልደን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምንገባበትምሥጢር ነው ። ዮሐ፡3፡5፡ ጥምቀት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ አለው ።(ማቴ 28፡19–20) ።
በጥምቀት ኃጢአት ይሠረያል የሐዋ ሥራ 2፡8 ። መንጻትና መቀደስም በጥምቀት ነው ። (1ኛ ጴጥ 3፡21፣ ቲቶ 3፡56) ።
በቤተክርስቲያናችን ሕፃናትን እናጠምቃለን በብሉይ ኪዳንሕፃናት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የሚኖራቸው በተገረዙ ጊዜ ነበር፣ በሐዲስ ኪዳንም ሕፃናት በሕፃንነት ዕድሜያቸው ተጠምቀው የክርስቶስ ቤተሰቦች ስለሚሆኑ በሕፃንነት ይጠመቃሉ እግዚአብሔር ሕፃናትን ከጸጋው ለይቷቸው አያውቅም ፡ ለምሳሌ ኤርምያስ የተቀደሰው በእናቱ ማኅፀን ነበር ። (ኤር 1፡5)። ዮሐንስ መጥምቁም በእናቱ ማኅፀንሳለ በመንፈስ ቅዱስ ተመልቶ ነበር ። (ሉቃ 1:15) ።
ጌታችን መድኃኒታችን በማስተማር ዘመኑ ሕፃናትን ባርኳቸዋል ይህም ሕፃናት ዕድሜያቸው ወደ እግዚአብሔር ከመቅረብ የሚከለክላቸው አለመሆኑን ያሳያል ። (ማቴ 19፡13-15 ፡ ማር 10፡13-15 ፣ ሉቃ 18፡15-17 ፣ የሐዋሥ 16፡33፡1 ቆሮ 1፡16)። በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት ወንድ ልጅ ሲወለድ በዐርባ ቀን ሴት ልጅ ስትወለድ በሰማንያ ቀን ይጠመቃሉ ።በብሉይ ኪዳን ወንድ ልጅ በተወለደ በዐርባ ቀኑ ወደ እግዚአብሔር ቤት ይገባ ነበር ፡ ሴት ልጅ ስትወለድም በሰማንያ ቀኗ ወደ እግዚአብሔር ቤት ትገባ ነበር ። (ዘሌዋ 12፡1 5። ሉቃ 2፡21 24) ። ሕፃናት ሃይማኖታቸውን ለመመስከር ስለማይችሉ ለወንድ ሕፃን የክርስትና አባት ለሴቲቱ ሕፃን የክርስትና እናት ይሰየሙላቸዋል ጥምቀት በመዝፈቅ ነው ። ጥምቀት በሥላሴ ስም ነው። (ማቴ 28፡19-20) ። ከመጠመቃቸው አስቀድሞ ለክርስቶስ ሲሉ በሰማዕትነት ደማቸውን ያፈሰሱ ሰማዕታትም በደማቸው እንደተጠመቁ ይቈጠራሉ ። (ማቴ 10፡32።16፡25) ።
ሥርዓተ ጥምቀት
– ጥምቀት ውሃ በብዛት ከሚፈስበት ጥምቀተ ባሕር በወንዝ ይፈጸማል ።– በቤተክርስቲያን ብዛት ያለው ውሃ ካልተገኘ በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ኩሬ በማበጀት ወይም ሰፊ ገንዳ በመሥራት ሰውነትን በሙሉ ሊያጠልቅ በሚችል ውሃ ይፈጸማል ።– ተጠማቂውን የሚያጠልቅ ውሃ በማይገኝበት ስፍራ የተገኘውን ውሃ ሦስት ጊዜ በእጅ ታፍነው ወይም በጽዋዕ ቀድተው መላ ሰውነቱን እንዲነካው በማድረግ ያጠምቋል ። (ዲድስቅልያ 34። ፍት· ነገሥ· አንቀጽ· 3)።
– ካህኑ የጥምቀቱን ጸሎት ከፈጸመ በኋላ ተጠማቂውን ይዞ «አሰግደከ/ኪ/ ለአብ ፡ እሰማዴከ/ኪ/ ለወልድ ፡ እሰግደ/ ኪ/ ለመንፈስ ቅዱስ» እያለ በዐራቱ መዓዝን ያሰግደዋል ። ሲያጠምቅም «አጠምቀከ/ኪ በአብ ፡ እምተከ/ኪ በወልድ አጠምቀከ/ኪ በመንፈስ ቅዱስ» እያለ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ያጠምቃል ። (ማቴ 28፡19 20) ።
– ተጠማቂው ወደ ጥምቀት ሲቀርብ ጠጉሩን ይላጫል ልብሱን ያወልቃል።
– ተጠማቂው ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ ተቀድሶ ሥጋውንና ደሙን ይቀበላል ። ይህም የሚሆንበት ምክንያት ቅዱስ ቁርባን የምሥጢራት ሁሉ መደመደሚያ ስለሆነ ነው ።
– ተጠማቂዎቹ አዋቂዎች ከሆኑ የተወሰነ የትምህርት ጊዜ ተሰጥቶ መሠረተ እምነት እንዲማሩና ዐውቀው አምነው እንዲጠመቁ ይደረጋል ።
– ወንዶች ወንዶችን፡ ሴቶችም ሴቶችን ብቻ ክርስትና ያነሣሉ ። (ፍት· ነገ· አን· 3 ዲድስቅ· 34 ። ዘኒቅ 24) ።-ማንኛውም ሰው ለመጠመቅ ከተወሰነው ጊዜ በፊት ለሞት የሚያሰጋሕመም ቢደርስበት ሥርዐተ ጥምቀት ይፈጸምለታል ። (ፍት· ነገ· ኣን· 3) ።
– ተጠማቂዎቹ ተምረው ዐውቀው የሚጸልዩ ከሆነ ራሳቸው ፡ የማይችሉ ከሆነ የክርስትና አባቶች ወይም እናቶች ጸሎተ ሃይማኖትን እንዲጸልዩላቸው ይደረጋል። ትምህርተ ሃይማኖትንም እያስተማሩ ለማሳደግ ቃል ይገባሉ።
– ከክርስቲያን ቤተሰብ የሚወለዱ ሕፃናት ወንዶች በ40 ቀን ሴቶች በ80ቀን ይጠመቃሉ ።
ነገር ግን ማንኛውም ሰው በክርስቶስ አዳኝነት ከአመነ በማንኛውምዕድሜ ከመጠመቅ አይከለከልም ።
– ጥምቀት በሥላሴ ስም ነው ። (ማቴ 28፡19)
– ጥምቀት አይደገምም (ሮሜ 6፡3 – 4 ። ኤፌ 4፡4-7)
– ጥምቀት በውሃ ብቻ ነው ። (ዮሐ 3፡5 ። ፍ· ነገሥ· 3) ።
– ተጠማቂው ከተጠመቀ በኋላ ማተብ በአንገቱ ይታሰርለታል ይህም የክርስቲያን ምልክትና መሊያ ነው ። ጥምቀት የክርስቶስ ሞት ምሳሌነው ፡ የክርስቶስ ሙቶ መቀበር ተጠማቂው ወደ ማጥመቂያው ለመግባቱ ምሳሌ ሲሆን ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ መነሣቱ ደግሞ ተጠማቂው ትንሣኤ ዘለክብርን የሚነሣ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ። (ዲድስቅ · 34 ሮሜ· 6:3-6) ።
ከዚህም ጋር ጥምቀት በመጽሐፈ ክርስትናና በፍትሐ ነገሥት በተወሰነው መሠረት ይፈጸማል ።
ሜሮን፡ ተጠማቂው ከማጥመቂያው ሲወጣ የሚቀባው ቅዱስ ዘይት ነው ፡ ሜሮን እንደ ጥምቀት ነው አይደገምም። በቅብዐተ ሜሮን ተጠማቂው የመንፈስ ቅዱስን ጸጋይቀበላል ። በሐዋርያት ጊዜ አማኞች ከተጠመቁ በኋላ በአንብሮተ እድ መንፈስ ቅዱስን ያሳድሩባቸው ነበር ። (የሐዋ ሥራ 20፡14-17) ። ቤተክርስቲያን እየተስፋፋች በሔደች ጊዜ ግን በአንብሮ እድ ፋንታ በሐዋርያተ መንበር የተተኩ ኤጴስ ቆጶሳት በቅዱስ ሲኖዶስ ሜሮንእያዘጋጁ አዲስ የተጠመቀ ሁሉ እንዲታተምበት ፈቀዱ ።
በሜሮን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ አለው ።
ሜሮን የሚቀባው ተጠማቂው ወዲያው ከማጥመቂያው ሲወጣ ነው። ሐዋርያት ሲያጠምቁ ሕፃኑንም ሆነ ሽማግሌውን ወዲያው በአንብሮተ እድ መንፈስ ቅዱስን ያሳድሩበት ነበር ። (የሐዋ ሥራ 8፤14-17 ፤ 19፡5-6) ። ሕፃናት ከተጠመቁ በኋላ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ወዲያውኑ በሜሮን ይቀባሉ። እንኳን ተወልደው በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ በመንፈስ ቅዱስ የከበሩ ሕፃናት እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል ። (ሉቃ 1፡15 ኤር 1፡18) ። ሜሮን የመቅባት ሥልጣን ያለው በሐዋርያ ትመንበር የተቀመጠው ኤጲስ ቆጶስ ነው። ቄሶችም እንዲቀቡ ተፈቅዷል።
በቤተክርስቲያናችን የምሥጢራት ሁሉ መደምደሚያ ቅዱስ ቁርባን ነው ። ቁርባን ማለት መሥዋዕት ማለት ነው ። ይኸውም ሰው ለእግዚአብሔር ያቀረበው ሳይሆን እግዚአብሔር ስለሰው ያቀረበው ነው። በብሉይ ኪዳን በምኵራብ የተሠዋው በግና ፍየል ሁሉ በአዲስ ኪዳን በቤተክርስቲያን ለሚሠዋው የክርስቶስ ሥጋና ደም ምሳሌ ነበር ። መልከ ጼዴቅ ለአብርሃም ያበረከተው ኅብስተ አኰቴት ጽዋዐ በረከት ። (ዘፍ 14፣18)። እሥራኤል የነጻነታቸው ዕለት የሠዉት መሥዋዕት የፋሲካችን በግ የክርስቶስ ሥጋ ምሳሌ ነበር ። ቁርባን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው ። (ማቴ 26፡26 ። ቀዳ ቆሮ 11፡23-25) ። ቄሱ ኅብስቱን በጻሕል ወይኑን በጽዋዕ አድርጎ ጸሎተ ቅዳሴውን ሲያደርስ ኅብስቱ ተለውጦ ሥጋመለኮት ፣ ወይኑ ተለውጦ ደመ መለኮት ይሆናል ። በቤተ ክርስቲያናችን ለምእመናን የምናቀብለው ከሥጋውም ከደሙም ነው።(ዮሐ 6፡54-58። ማቴ 26:27)።
– ቄሱ ሥጋውን ሲያቀብል ዲያቆኑ ደሙን በዕርፈ መስቀል ያቀብላል ።
– ወደ ቤተክርስቲያን መምጣት ለማይችሉ በሽተኞች በዕለቱ ተቀድሶ በቤታቸው እንዲቈርቡ ይደረጋል ።
– መሥዋዕት ከዕለቱ አያልፍም ፣ አይውልም ፣ አያድርም ። ቁርባን የሚቈረበው ሳይበላ ሳይጠጣ ቢያንስ ለ15 ሰዓት በመጾም ነው ።
– በቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ቁርባን ፍጹም የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው። (ዮሐ 6፡51-55) ።
እንደ ሌሎቹ ምሥጢራት ሁሉ ምሥጢረ ቁርባንን የሚፈጽሙ በሐዋርያት መንበር የተቀመጡ ጳጳሳት ነበሩ ። ቤተክርስቲያን እየተስፋፋች ስትሔድ ግን ለቀሳውስት ፈቀዱላቸው ፣ ዲያቆናት የጳጳሱና የቄሱ ረዳቶች ናቸው ። ራሳቸውን በንስሓ የመረመሩና ያጸዱ ምእመናን ሥጋውን ደሙን መቀበል ይችላሉ ራሳቸውን በንስሓያላዘጋጁ ግን ቢቀበሎም ዕዳ ይሆንባቸዋል ። (ቀዳ ቆሮ 11፡28-29 ዮሐ· አፈ ወርቅ ቅዳሴ)።
ክህነት፦ የቤተክርስቲያን ከፍተኛው ከፍተኛው መንፈሳዊ መዐርግ ነው ። ክህነት መጽሐፍ ቅዳሳዊ መሠረት አለው። (ማቴ 28፡19 ፣ 20 ። ኤፌ 4፡11 ። የሐዋ ሥራ 28፡20) ።
በቤተክርስቲያናችን የክህነት መወርጋት ሦስት ናቸው ፡ እነሱም፡ ዲቁና ፡ ቅስናና ጵጵስና ናቸው ።
1ኛ ዲያቆን፡
ሀ) ከማግባቱ በፊት ዲቁና ይሾማል ።
ለ) አግብቶ ወይም መንኩሶ የቅስና መዐርግ ይቀበላል ።
ሐ) አገልግሎቱም የቄስና የጳጳስ ረዳትነት ነው ።
መ) የሚሾመው በጳጳስ ነው ።
ሠ) በቤተ ክርስቲያናችን ከሙሉ የዲቁና መዐርግ በፊት ድባት ለተልእኮ የሚያበቁ 3 መዓርጋት የሚሰጡ በአንብሮተየሚታሰበ እድ ሳይሆን በቃለ ቡራኬ ብቻ ነው ።
ረ) ዲያቆናት በአንብሮተ እድ ብቻ ይሾማሉ ።
ሰ) ሥልጣነ ክህነት ለመቀበል ዋጋ አይሰጥም ። (የሐዋ. ሥራ 8፡18-26)
ሸ) ክህነት በዘር ሐረግ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ጥሪና በቤተክርስቲያን ቀኖና ነው።
2ኛ ቄስ፡
ዲያቆኑ ካገባ ወይም ከመነኮሰ በኋላ የቅስና ሥልጣን ይቀበላል። አገልግሎቱም ሥልጣነ ክህነት ከመስጠት ሜሮን ከማዘጋጀት አዲስ ቤተክርስቲያንና አዲስ መንበር አዲስ ጽላትና ሌሎችንም አዳዲስንዋየ ቅድሳት ከመባረክ በቀር ሌላውን ሁሉ ይፈጽማል ።
በድንግልና የቀሰሰ ከሆነ ወደ ጵጵስና መዐርግ መድረስ ይቻላል ፡ ባለሕግ ከሆነ ግን በዚህኛው መዐርግ ብቻ ይወሰናል ። ይህም በአንብሮተ እድና በንፍሐት በጳጳስ ይሾማል ።
3ኛ ጳጳስ፡ (ኤጲስ ቆጶስ)
ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾመው በድንግልና የመነኮሰ ካህን ነው ። የሚሾመው በመላ የሲኖዶስ አባላት ነው። በችግር ጊዜግን ከሁለት ባላነሱ ኤጴስ ቆጶሳት በአንብሮተ እድና በንፍሐት ይሾማል ። አገልግሎቱም ምሥጢራትን ከመፈጸም ጋር ጠቅላላ የቤተክርስቲያን መሪና ጠባቂ ነው ። እነዚህን መዐርጋት የሚቀበሉ ሁሉ የሚያሟሏቸው ግዴታዎች አሏቸው ።
ሀ) ጤንነት ያላቸው
ለ) ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋት በቂ ትምህርት ያላቸው
ሐ) በጠባይ የተመሰገኑ መሆን አለባቸው
መ) ወደ መዐርገ ክህነት የሚቀርቡ ሁሉ በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት ወንዶች ብቻ ናቸው ።
ሠ) ክህነት አይደገምም ወይም አይታደስም በድጋሚ ክህነት የሚቀበል ወይም የሚሰጥ ሁለቱም ከክህነታቸው ይሻራሉ ። (የሐዋርያት ቀኖና 68) ። ክርስቶስ ለቤተክርስቲያኑ የተወሰኑ ሰዎችን ለክህነት መርጦአል ። (ሉቃስ 6፡12፡13 ። ዮሐ 20፡19-25) ። ለሌላ ያልተሰጠ ልዩ ሥልጣንም ሰጥቷቸዋል ። (ማቴ18፡18) ። በዕርገት ሲሰናበታቸው እስከ ዓለም ፍፃሜ እንደማይለ ያቸው ቃል ገብቶላቸዋል ። (ማቴ 28፡20) ። ሲያርግም ጠቅላላመዐርገ ክህንነትን ሾሟቸው ዐረገ ። (ሉቃስ 24፡51) ።
ከሐዋርያት አባልነት በወጣው በይሁዳ ምትክ ለመምረጥ በሲኖዶስ ተሰብስበው ለቤተክርስቲያን አገልግሎት ማትያስን መምረጣቸው የሐዋርያት አገልግሎት ከሌላው ሕዝባዊ አገልግሎት የተለየመሆኑን ያሳያል ። (የሐዋ· ሥራ 1፡15–26) ።
የክርስቲያኖች ጋብቻ በቤተክርስቲያን ምስክርነት የሚፈጸም ጸጋመንፈስ ቅዱስንም የሚያሰጥ ስለሆነ ከሰባቱ ምሥጢራት አንዱ ነውጋብቻ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው ። (ዘፍ· 1፡27-28 ። 2፡18 ማቴ· 19፡ 4-6) ።
በቤተክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት ክርስቲያናዊ ጋብቻ ከመፈጸሙ በፊት የሚከተሉት ግዴታዎች መሟላት አለባቸው ።
- ጸጋ መንፈስ ቅዱስን በእኩልነት የሚቀበሉ ስለሆኑ ሁሉም ክርስቲያን መሆን አለባቸው ።
- ሁለቱም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባላት መሆን አለባቸው።
- ሁለቱ አንድ ካልሆኑ ግን ጋብቻው ከመፈጸሙ በፊት የቤተክርስቲያናችን አባል መሆን ግዴታ ነው ።
- ከጋብቻ በፊት ሥጋዊ ግንኙነት አይፈቀድም ።
- ለጋብቻው ሁለቱም ፈቃደኞች መሆን አለባቸው ።
- በቤተሰብ መካከል የሥጋዊም ሆነ የመንፈሳዊ ተዘምዶ ገደብ በጋብቻ እንዳይፈርስ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ መከበር አለበት (ዘሌዋ፡18፡6-21 ። ዘዳግም 7፡3-4)።
– በሞት ፡ በዝሙት ካልሆነ በቀር ከሁለቱ አንዱ ተለይቶ ለማግባት አይችልም ። (ማቴ 19፡6 ፤ 9 ።)
– የክርስቲያኖች ጋብቻ የክርስቶስና የቤተክርስቲያን አንድነት ምሣሌ ስለሆነ አይፈርስም ። (ኤፌሶን 5፡32)።
– የተክሊልን ምሥጢር የሚፈጽሙ ጳጳሳትና ቀሳውስት ናቸው
– ተክሊል ያለሥጋ ወደሙ አይፈጸምም ። (ፍት· መን· 24 ቁ·899) ።
– በጋብቻ ጊዜ የወላጆች ፈቃድ መጨመር አለበት ።
ንስሓ፦ መጸጸት ፣ መመለስ ፣ ከኃጢአት መንጻት ማለት ነው። ክርስቲያኖች በጥምቀት እንደገና የተወለዱ ቢሆኑም ሰው ሆኖ ወደ ኃጢአት ማዘንበል የማይቀር ነውና ፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን መምህረ ንስሓ ሊኖረው ይገባል ።
– ክርስቲያኖች ወደ መምህረ ንስሓ እየሄዱ ኃጢአታቸውን ይናዘዛሉ ። (ዘሌ· 14፡31 ማቴ· 8፡4 ኤጲፋንዮስ ሃይ አበ ምዕ 59 ቁ· 20) ። ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ያደረጉት ሙከራና ኃጢአታቸውንም መናዘ ዛቸው ጸጋ እግዚአብሔርን ያሰጣቸዋል ። ሥጋውን ደሙን ተቀብለው ወደ ቀደመ ክብራቸው ይገባሉ ።
– ኑዛዜ መቀበልና ማስተሥረይ የሚገባቸው ጳጳሳትና ቀሳውስት ብቻ ናቸው ። ንስሓ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው ። (ማቴ 8፡4 ፡ 16፣19) ። ንስሓ ተነሳሒው በመምህረ ንስሓው ፊት ቀርቦ ኃጢአቱን በመናዘዝ የሚያፈሰው እንባ የኃጢአቱን ክብደት እያስታወሰ የሚያሳየው ጭንቀት በመንፈስ ቅዱስ እንደገና እንዲታደስ ያደርገዋል ። (አትና ቴዎስ ቅዳሴ )
– ንስሓ ከሚደጋገሙ ምሥጢራት ጋር የሚቆጠር ነው ። ከነቢያት ጀምሮየመጥምቁ ዮሐንስ ፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና የተከታዮቹ የሐዋርያት የትምህርት ዋና ዓላማ ሰው ሁሉ በንስሓ እንዲመለስና ወደእግዚአብሔር መንግሥት እንዲገባ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” የሚል ነበር ። ዛሬም ቤተክርስቲያን ስለ ንስሓ የምታስተምረው ይህንኑ መሠረት አድርጋ ነው ። (ዘካ· 1፡3 ። ማቴ· 3:1-2 ። 4:17) ።
ቀንዲል ፦ቤተክርስቲያናችን ከምትገለገልባቸው ሰባት ምሥጢራት አንዱ ነው ። ይህ ምሥጢረ ቀንዲል ለበሽተኞች የሚቀባ ነው ። ቀንዲል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው ። (ማር· 6፡13 ያዕቆብ 5፡13-15) ።በቤተክርስቲያናችን የቀንዲል መጽኃኒትነት ለሥጋ ብቻ ሳይሆን ለነፍስም ስለሆነ በኃጢአት ደዌ ለተያዘ ቀንዲል ይደረግለታል ። የቀንዲል ምሥጢር የሚፈጸመው በጳጳሳትና በቀሳውስት ነው ።
ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ለእያንዳንዳቸው የሚፈጸም የእየራሳቸው የሆነ መጽሐፈ ጸሎትና የአፈጻጸም ሥርዐት አላቸው ሁሉም ምሥጢረ ቤተክርስቲያን የቤተክርስቲያኒቱ ሥርዐተ አምልኮ ማስፈጸሚያና የሃይማኖት መመሪያ ነው ።
እነዚህ ምሥጢራት ሁሉም በቤተክርስቲያን ይፈጸማሉ ፡ ሆኖምእንደእየሁኔታው በሌላም ቦታ ይፈጸማሉ ፡ ውግዘት የለበትም ። የሁሉም ምሥጢራት ዋና ዓላማ ሰውን ለማዳን ነው ።
መዕራፈ ፭ ቅዱሳት መጻሕፍት
ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ በመንፈሰ እግዚአብሔር የተጻፉ ወይም እስተንፋሰ እግዚአብሔር ናቸው ። በሌላም አገላለጽ መጻሕፍት አምላካውያት ይባላሉ ። (ፍት· ነገ· አን· 2) ። ቅዱሳት መጻሕፍት እስትንፋሰ እግዚአብሔር ለመሆናቸው ወይም በመንፈሰ እግዚአብሔር ለመጻፋቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ2ኛ ጢሞ 3·17 «የእግዚአብሔር መንፈስያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል» ብሎ ጽፎአል ። ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያም «ቅዱሳት መጻሕፍት እስትንፋሰ እግዚአብሔርናቸው» ብሎአል ። (ቄር· ሃይ· አበ 78፡67) ።
በመሆኑም በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈው ሁሉ ፍጹም እውነትነው ፡ ሊለወጥ ሊሻሻል ፡ ሊጨመርበት ወይም ሊቀነስለት የማይቻልነው። በመንፈሰ እግዚአብሔር የተቃኙ ቅዱሳን ሰዎች ጽፈውታልና (2ጴጥ· 1፡20 ። ማቴ 5፡18 ። ሉቃ· 16፡17) ። ልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳት መጻሕፍትን «እንዲህ ብለህ ተናገር! እንዲህ ብለህ ጻፍ» እያለ ድምፁን በማሰማት ፡ በራእይ እየተገለጸ ፣በልቡና እየቀረፀ እንዲጻፉ ማድረጉ ተገልጦአል ። (ዘጸአ· 34፡27 ። ዘዳግ· 31፡19 ። ኢሳ· 8፡1) ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በቀኖና የተቀበለቻቸው የብሉያትና የሐዲሳት መጻሕፍት ቁጥር 81 ነው ።
ሀ) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት
1· ኦሪት ዘፍጥረት
2· ኦሪት ዘጸአት
3· ኦሪት ዘሌዋውያን
4· ኦሪት ዘኁልቁ
5· ኦሪት ዘዳግም
6· መጽሐፈ ኢያሱ
7· መጽሐፈ መሳፍንት
8· መጽሐፈ ሩት
9· 1ኛና 2ኛ ሳሙኤል
10· 1ኛና 2ኛ መጽሐፈ ነገሥት
11· 1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል
12· 2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል
13· መጽሐፈ ኩፋሌ
14· መጽሐፈ ሄኖክ
15· መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ
16· ዕዝራ ካልእና ዕዝራ ሱቱኤል
17· መጽሐፈ ጦቢያ
18· መጽሐፈ ዮዲት
19· መጽሐፈ አስቴር
20· መጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ
21· 2ኛና 3ኛ መጽሐፈ መቃብያን
22· መጽሐፈ ኢዮብ
23· መዝሙረ ዳዊት
24· መጽሐፈ ምሳሌ
25· መጽሐፈ ተግሣጽ
26· መጽሐፈ ጥበብ
27· መጽሐፈ መክብብ
28· መጽሐፈ መኃልየ መኃልይ
29· መጽሐፈ ሲራክ
30· ትንቢተ ኢሳይያስ
31· ትንቢተ ኤርምያስ
32· ትንቢተ ሕዝቅኤል
33· ትንቢተ ዳንኤል
34· ትንቢተ ሆሴዕ
35· ትንቢተ አሞጽ
36· ትንቢተ ሚክያስ
37· ትንቢተ ኢዩኤል
38· ትንቢተ ዐብድዩ
39· ትንቢተ ዮናስ
40· ትንቢተ ናሆም
41· ትንቢተ ዕንባቆም
42· ትንቢተ ሶፎንያስ
43· ትንቢተ ሐጌ
44· ትንቢተ ዘካርያስ
45· ትንቢተ ሚልክያስ
46· መጽሐፈ ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን
ድምር 46
ለ) የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት
1· የማቴዎስ ወንጌል
2· የማርቆስ ወንጌል
3· የሉቃስ ወንጌል
4· የዮሐንስ ወንጌል
5· የሐዋርያት ሥራ
6· ወደ ሮሜ ሰዎች
7· ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1ኛ
8· ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2ኛ
9· ወደ ገላትያ ሰዎች
10· ወደ ኤፌሶን ሰዎች
11· ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች
12· ወደ ቆላስይስ ሰዎች
13· ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 1ኛ
14· ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 2ኛ
15· ወደ ጢሞቴዎስ 1ኛ
16· ወደ ጢሞቴዎስ 2ኛ
17· ወደ ቲቶ
18· ወደ ፊልሞና
19· ወደ ዕብራውያን
20· የጴጥሮስ መልእክት 1ኛ
21· የጴጥሮስ መልእክት 2ኛ
22· የዮሐንስ መልእክት 1ኛ
23· የዮሐንስ መልእክት 2ኛ
24· የዮሐንስ መልእክት 3ኛ
25· የያዕቆብ መልእክት
26· የይሁዳ መልእክት
27· ራእይ
ሐ) የሥርዓት መጻሕፍት
1· ሥርዓተ ጽዮን
2· ትእዛዝ
3· ግጽው
4· አብጥሊስ
5· 1ኛ መጽሐፈ ኪዳን
6· 2ኛ መጽሐፈ ኪዳን
7· ቀሌምንጦስ
8· ዲድስቅልያ
ድምር 35
የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ድምር 46
የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ድምር 35
ጠቅላላ ድምር 81
ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት የተለያየ አቈጣጠር ቢኖርም የኢትዮጵያኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምትቀበላቸውና በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ ተዘርዝረው የሚገኙ መጻሕፍት ከዚህ በላይ የተመለከቱት 81መጻሕፍት ናቸው ።
ከነዚህም ጋር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በብሉይና በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ የብሉያትና የሐዲሳትን ምሥጢራት አብራርተውና አጉልተው የሚገልጡ በልዩ ልዩ ቅዱሳን አበው የተደረሱ የሃይማኖት ፣ የትምህርት የጸሎት መጻሕፍት ከብሉያትና ሐዲሳት ተውጣጥተው የተደረሱ የቅ/ያሬድ የፀዋትወ ዜማመጻሕፍት ሌሎችም የአገልግሎት መጻሕፍት አሉአት ።
ቅዱስ ያሬድ
ቅዱስ ያሬድ በኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር በ505 ዓ·ም· የተነሣ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ነው ። ቅ/ያሬድ በዓለም በሚታወቅበት ሙያውና ዕውቀቱ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ የመንፈሳዊ ዜማ ደራሲ ፣ የቅኔ ተመራማሪ ኪሩቤልን በሚያስመስለው ጣዕመ ዝማሬ የተወደደና ድምፀ መልካም ማሕሌታዊ ነው።
ቅዱስ ያሬድ ድጓ ፡ ዝማሬ ፡ መዋሥዕትና ምዕራፍ የተሰኙ የዜማመጻሕፍት አሉት ። የብሉያት ፡ የሐዲሳትና የሊቃውንት መጻሕፍት ትርጓሜም ሊቅ ነው ። ከነዚህ ከብሉያት ከሐዲሳትና ከሊቃውንት መጻሕፍት ለጸሎትና ለማሕሌት የሚስማሙትን ቃላት እየመረጠ ፥ ምሥጢራትን ከትርጓሜ እያስማማ ዜማዎቹን በዐራቱ ክፍላተ ዘመን በመፀው ፥ በሐጋይ ፥ በጸደይና በክረምት በመክፈል የየወቅቱን የተፈጥሮሥነ ባሕርይ በአንክሮና በምስጋና በሚገለጽ ጣዕም እንዲዘመሩና እንዲጸለዩ ያደረገ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ነው ። ዜማውንም ግእዝ ፥ዐዝልና አራራይ በሚል በ3 የዜማ ስልት ከፍሎ ዘምሮታል ።
ሊቁ ቅ/ያሬድ የዜማ ድርሰቱን ያዘጋጀው ከ540–560 ዓም ባለውዘመን ነው ። ማሕሌታዊው ቅ/ያሬድ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍሎች ለ 11ዓመታት እየተዘዋወረ ሲያስተምር ፣ ቤተክርስቲያንን ሲያገለግልናሲያስገለግል ቈይቷል ።
በመጨረሻም በሰሜን ተራራዎች ሥር ካሉት ገዳማት በአንዱ ዋሻውስጥ ገብቶ በጾም በጸሎት፣ በብሕትውና ዘመኑን አሳልፎአል ። ሊቁ ቅ/ያሬድ እስከዛሬ ኅልፈትና ውላጤ ያላገኘው ፣ በጣዕመ ዝማሬውና በምልክቱ ልዩ የሆነ የዜማ ድርሰቱን ለኢትዮጵያ ያበረከተ ታላቅኢትዮጵያዊ ሊቅ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዝክረ ስሙን በጥንቃቄ ጠብቃ ፤ በስሙ ጽላት ቀርፃ ፣ ቤተክርስቲያንን አንፃ ፣ ገድሉን ጽፋ ታከብረዋለች።
ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት ከቅዱስ ያሬድና ከሌሎችም መጻሕፍት ሌላ በቀደምት የጋራ አባቶች የተደረሱና ተተርጉመው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ይገኙባቸዋል ። የእመቤታችን የቅ/ድንግል ማርያምን ተአምር ፡ንጽሕናዋንና ቅድስናዋን የሚያረጋግጡ ፥ የቅዱሳን መላእክትን ፡ ተልእኮ የቅዱሳን ጻድቃንና የሰማዕታትን የነቢያትንና የሐዋርያትን ተአምርና ገድል የሚገልጡ የተሰጣቸውን ቃል ኪዳን ጸጋና ክብርየሚናገሩ ገድላትና ድርሳናት የተአምራት መጻሕፍት አሉአት ።
ምዕራፍ ፮ ትውፊት
ትውፊት ማለት ከጥንት ጀምሮ በቤተክርስቲያን በኩል ቃል በቃል ሲነገር የመጣ በቃልም በጽሑፍም ከአበው ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረና የሚኖር ማለት ነው ።
የሰው ልጅ እምነቱንና ሥርዓቱን ባህሉንና ታሪኩን በጽሑፍ ከመያዙ አስቀድሞ ከአዳም እስከ ሙሴ ቃል በቃል እየተነገረ በተላለፈ ትውፊት መቈየቱ ይታወቃል ። ይህም የትውፊት አመጣጥ መሠረት ነው።
ትውፊት በቅዱሳት መጻሕፍት ያልተጻፉትን ከአበው ቃል በቃል የተላለፉትን የእምነት የሥርዓት ፣ የትምህርትና የታሪክ ውርሶች እያጐላ ያቀርባል ። መሠረታቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ሆነው በትርጉም ያልተገለጡትን በተግባር ያሳያል ። ትውፊት ከቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢርና ትርጉም ጋር የሚቃረን አይደለም ።
ትውፊት ትምህርተ ሃይማኖትን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ባህልንና ታሪክን ብቻ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ ሳይፋለስና ሳይለወጥ የተላለፈውን የሥርዓተ አምልኮት አፈጻጸምን ሁሉ ያካትታል ።
የቤተክርስቲያን እምነትና ትምህርት በጽሑፍ ሳይሆን ይሰጥ የነበረው በቃል ነው ። የተጻፈም በቃል ሲነገር የነበረው ነው ። “ማመን ከመስማት ነው ፣ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው” ተብሎ ተጽፎአልና (ሮሜ 10፡17)።
ከነቢያት እየጻፉ ያስተማሩ መኖራቸው ቢታወቅም ብዙዎቹ በቃል አስተምረዋል ። ሐዋርያትም ጌታችን ወደ ዓለም በላካቸው ጊዜ በቃል አስተምረዋል ። (ማቴ· 28፡19። ማር· 16፡15)።
ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትና ተአምራት ጥቂቱን ብቻ መጻፋቸውን በግልጥ ተናግረዋል ። (ዮሐ· 20፡30። ዮሐ 21፡25)። ራሳቸውም ያስተማሩትን ትምህርትና ያደረጉትን ተአምር በሙሉ አልጻፉም ። (2ዮሐ· ቁ· 12፡3 ዮሐ· ቁ· 13–14)።
ስለ ትውፊት ቅዱሳት መጻሕፍት በብዙ ቦታ ይመሰክራሉ ። (1ቆሮ· 11፡2 ፣ 23 ። 15-1-3። 1ተሰ· 2፡13። 2ተሰ· 2፡15)። ስለዚህ ቅዱስ መጽሐፍና ትውፊት ይደጋገፋሉ ትውፊት መጽሐፍ ቅዱስን ይጠብቃል ፣ይተረጉማል ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ የቀረውንም ይሞላል ። ይህንንም ለማረጋገጥ ቅዱስ ጳውሎስ በ2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡8 ላይ «ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን እንደ ተቃወሙት» ሲል ይናገራል ። የኢያኔስና የኢያንበሬስ ስምበኦሪቱ አልተጻፈም እንደዚሁም በሐዋርያት ሥራ 20፡35 ላይ «ጌታችን እንደተናገረ ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው» በማለት የተናገረው በአራቱም ወንጌሎች ተጽፎ አይገኝም ። ቅዱስ ጳውሎስ እነዚህን ሁሉ የጻፋቸው በትውፊት በተገኘው ትምህርት ነው ።
እንደዚሁም አራቱን ወንጌሎች የጻፉ ወንጌላውያን ማቴዎስ ፣ ማርቆስ ፣ ሉቃስና ዮሐንስ መሆናቸው የተገለጠው በትውፊት ነው ።
ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስም «መስቀል ማድረግና በመስቀል ማማተብ ፣ በጸሎት ጊዜ ፊትን ወደ ምሥራቅ ማዞርና ቀጥ ብሎ መቆም የመጠመቂያ ውሃን መባረክ ፣ ተጠማቂውን በዐራት መዐዘን ማሰገድ ፣ተጠማቂዎችን ሜሮን መቀባት ፣ ሰይጣንና ሠራዊቱን «እከህደከ» ማሰኘት ትውፊት እንደሆነ ተናግሮአል ። (ባስልዮስ ድርሳን 27፡66)።
በቤተክርስቲያናችንም ትምህርትና ሥርዓት ፣
– መስቀል ማሳለም ፣
– ለሥዕልና ለመስቀል መስገድ
– ማተብ ማሰር
– በቤተክርስቲያን ዕጣን ማጠን
– በተለያዩ የአምልኮት ሥርዓት ማስፈጸሚያ በሆኑ ንዋያተ ቅድሳት ማገልገል
– የቤተክርስቲያን ሕንፃ አሠራርና የውስጥ ክፍሎች አከፋፈል ።
– ልብሰ ተክህኖና የመሳሰሉትም ሁሉ በትውፊት የተገኙ ናቸው ።
ስለዚህ ቤተክርስቲያናችን ጥንታዊት ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ስለሆነች ከቀደምት አበው ሲያያዝ የመጣና ሲሠራበት የኖረውን ትውፊት ጠብቃና አክብራ ትገለገልበታለች ።
ምዕራፍ ፯ ክብረ ቅድስት ማርያም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስና ድንግልና ፡ ቃል ኪዳንና አማላጅነት በሰፊው የታወቀ ነው ።
ቅድስና
አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ከአዳም ዘር የተላለፈ ኀጢአት (ጥንተ አብሶ) ያላገኛት ፣ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት ገና ከመወለዷ አስቀድሞ በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር የነበረች ፡ በሰው ልማድና ጠባይ ከሚደርሰው ሥጋዊ አሳብና ፈቃድ ሁሉ የተጠበቀች ፡ ከተለዩ የተለየች ንጽሕት ቅድስተ ቅዱሳን ናት መሓል· 4፡7 ።«ምልዕተ ፀጋ ምልዕተ ክብር ሆይ! ደስ ይበልሽ» ተብላ በቅዱሳን መላእክት አንደበት በቅድስናዋ ተመስግናለች ፡ ትመሰገናለችም ። (ሉቃ· 1:28-30) ።እመቤታችን በውስጥ በአፍኣ በነፍስ በሥጋ ቅድስት ስለሆነች እግዚአብሔር ለልጁ ማደሪያ መርጧታል ፡ ማኅደረ መለኮት እንድትሆንአድርጓታል ። አምላክን ለመውለድ ያስመረጣትና ያበቃት ፡ ድንግልናዋንጽሕናዋ ነው ። (ሕርያቆስ· ቅዳሴ ፡ 45 መዝ· 132፡13)። ንጽሐ ሥጋንጽሐ ነፍስ ንጽሐ ልቡና ለእመቤታችን ገንዘቦቿ ናቸው ።
ድንግልና
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ከተለዩ የተለየች ከከበሩየከበረች የሚያደርጋት ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷ ነው (ማቴ 1፡18-20)። እመቤታችንጌታን ከመፅነሷ በፊት ፡ በፀነሰች ጊዜ ፡ ከፀነሰች በኋላ ፡ ከመውለዷ በፊት በወለደች ጊዜ ከወለደች በኋላ ድንግል ናት ። እመቤታችን ከሌሎች ሴቶች ሁሉ ተለይታ እግዚአብሔር ከፈጠራት ጀምሮ በአሳብ ፡ በመናገር ፡ በመሥራት ፡ ንጽሐ ጠባይዕ ያላደፈባት ንጽሕት ድንግል ናት ።ቴዎዶጦስ ዘእንቆራ ሃይ· አበ· ም· 53፡22 ድንግል የሚለው ቃል በርግጥ ቅድስናዋን ንጽሕናዋን ያመለክታል ። በዓለም ከነበሩና ከሚኖሩ ሴቶች እናትነትን ከድንግልና እንደ እመቤታችን ድንግልናን ከእናትነት : አስተባብራ የተገኘች ሴት የለችም ። እመቤታችን ዘለዓለም ድንግል ናት ቅዳሴ ባስልዮስ 23 መሐልይ 4፡15 ሕዝ· 44፡3 ወንጌላዊ ሎቃስ «ቅዱስ ገብርኤል ወደ አንዲት ድንግል ተላከ ፡ የዚያችም ድንግል ስም ማርያም ነው» በማለት ስለ ድንግልናዋ ተናግሯል። (ሉቃ· 1፡27) ። እመቤታችን የደናግል ሁሉ መመኪያ ናት ። (ኤፍሬም 6፡3) ።
ክብረ ድንግል
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከመላእክት ትበልጣለች ፡ በክብርም ፡ በአማላጅነትም ፡ ከቅዱሳን ሁሉ ቅድሚያ ያላት ናት ። ሌሎች ሴቶች የሚከበሩ ነቢያትን ሓዋርያትን ጻድቃን ሰማዕታትን ወለዱ ተብለው ነው ። እሷ ግን የምትከበረው እመ አምላክ ፡ ወላዲተ አምላክ ተብላ ነው ። በመሆኑም ድንግል ማርያም ከፍጡራን በላይ ፡ ከፈጣሪ በታች ክብሯ ከፍ ያለ ነው ። የአክብሮት ወይም የጸጋ ስግደትይሰገድላታል ። (ዮሐ· አፈ· ሃይማ·አበ· ምዕ· 28፡36-39) ።በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ«ሉቃ 1 27»
ምስጋና
ስለ እመቤታችን ክብርና ልዕልና ከሥጋዌ አስቀድሞ ብዙ ትንቢቶች ተነግረዋል ። አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የመውለድዋ ምሥጢርም በነቢያት የተነገረ ነው (መዝ· 132፡13 ፡ ኢሳ· 7፡14።ሕዝ· 44፡3)።
የቤተክርስቲያን አበው ሊቃውንት በየዘመናቸው በመንፈስ ቅዱስ እየተቃኙ በውነት አንቺ ቅድስት ነሽ ንጽሕት ነሽ እያሉ ስለ ዘለዓለማዊ ንጽሕናዋና ቅድስናዋ በውዳሴያቸው ፡ በድርሰታቸው አመስግነዋታል። ውዳሴ ፡ ቅዳሴ ደርሰውላታል ። ከዚያውም ሁሉ እነ ቅ/ኤፍሬም ፣ አባ ሕርያቆስ ቅ/ዮሐንስ አፈወርቅና አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ቅድስት ንጽሕት እያሉ በሠፊው አመስግነዋታል ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ቅድስናዋን ንጽሕናዋን ትመሰክራለች ፡ ታመስግናታለችም ። የእመቤታችን ሕይወት ከእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ጋር የተዋሐደ ነው ።
ኖኅ በእግዚአብሔር ጥበብ የሠራት መርከብ ፣ ራሱንና ቤተሰቡን ከጥፋት ውሀ በማዳን ለሰው ዘር መትረፍ ምክንያት እንደሆነች ሁሉ ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስን በመውለድ ምክንያተ ድኂን ሆኖለች። በቤተክርስቲያናችን እምነትና ትምህርት ድንግል ማርያም ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች ሆና ትከበራለች ። በመዝሙራችንም ሆነ በቅዳሴአችን ከስመ ሥላሴ ቀጥለን የምንዘምረው የድንግል ማርያምን ውዳሴ ነው ።
አምላክ ሰው በመሆኑ ለሰው ልጆች የዋለውን ውለታ፦ በበረትመወለዱን ፣ በጨርቅ መጠቅለሉን ፣ ስደቱን ፣ መንከራተቱን ፣ ሕማሙን ፣ ስቅለቱንና ሞቱን በምናስብበት ጊዜ ድንግል ማርያምን መለየት አይቻልም ።
«ደስ ያለሽ ምልዕተ ክብር ሆይ ፣ ደስ ይበልሽ ከሴቶች ተለይተሽአንቺ የተባረክሽ ነሽ ፣ ··· በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና ··· መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል ፣ የልዑል ኃይልም ይጋርድሻል ተብሎ የተመሰገነ ከእርስዋ በቀር ማንም የለም ። (ሉቃ 1፡28–35) ።ከዘመዶችዋም ወገን ቅድስት ኤልሣቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝታ «አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ ፣ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከነው” ብላ ከማመስገኗ በላይ የጌታዬ እናት ወደኔ ትመጪ ዘንድ እኔ ምንድነኝ? በማለት ወላዲተ አምላክ መሆኗን መስክራለች ፣ ከእግዚአብሔር ስለእርስዋ የተነገረው ሁሉ እንደሚፈጸም አምና የምትቀበል ንዕድ ክብርት እንደሆነች አረጋግጣለች ።
የሰላምታ ድምፅዋን በሰማችም ጊዜ በማኅፀኗ የነበረው ፅንስ (ዮሐንስ) በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ በመዝለል ከቅድስት ድንግል የሚወለደው አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን አረጋግጦአል ። ራሷ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ከእንግዲህስ ወዲህ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ነሽ እያሉ ያመሰግኑኛል» በማለት ተናግራለች ። (ሉቃ· 1፡48) ።
በዚሁ መሠረት በልጅዋ ያመኑ ክርስቲያኖች ሁሉ የንጽሕናቸው መሠረት ፡ የድንግልናቸው መመኪያ ፣ የደኅንነታቸው ምክንያት አድርገው ያመሰግኑአታል ።
የአማላጅነት ቃል ኪዳን
ቤተክርስቲያናችን ስለ እመቤታችን አማላጅነትና ቃል ኪዳን የምታስተምረው በቅዱስ መጽሐፍ በተጻፈው ቃልና ፍጹም በሆነ ሐዋርያዊ ትውፊት ነው ። እመቤታችን የእናትነት ክብርና የእማላጅነት ቃል ኪዳን ከልጅዋ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቀብላለች ፡ በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤት ልጅዋ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃውን ወደ ወይን ለውጦ የመጀመሪያውን ተአምር ያደረገው በእመቤታችን አማላጅነት ነው ። (ዮሐ· 2፡1-5) ። ጌታ በመስቀል ላይ ሳለ «እነሆ ልጅሽ» (ዮሐንስ 19፡26) ብሎ ቤተክርስቲያንን ለርሷ «እነሆአት እናትህ» ብሎ እርሷን ለቤተክርስቲያን አደራ ሰጥቷል ። እመ አምላክ ወላዲተ አምላክ መሆኗን አምነው «ሰአሊ ለነ ቅድስት» ቅድስት ሆይ ለምኝልን እያሉ ስሟን የሚጠሩትን ሁሉ እንደሚምርላት የማይለወጥ ቃል ኪዳን ተቀብላለች ።
ስለዚህ ቤተክርስቲያን ከልጅዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለችውን አደራ በመጠበቅ ቅድስት ማርያም
የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ
የአምላክ እናት
ዘለዓለም ድንግል
ቅድስተ ቅዱሳን ስለሆነች
ቅዱስ መጽሐፍም ይህን ክብሯን ስለሚመሰክር፣
ቅዱሳን መላእክትና ደቂቀ አዳም ስላከበሯት ፡ በየጊዜው በስሟስለሚደረጉ ተአምራት ታከብራታለች። ታመሰግናታለች ፡ ትማፀንባታለች፡ (ያዕቆብ ዘሥሩግ ቅዳሴ ሐዳፌ ነፍስ፡99) እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲተላለፍ በመጣው ትውፊት በተገለጠው መሠረት በ64 ዓመት ዕድሜዋ በጥር 21 ቀን ዐርፋለች ። መላእክት ሥጋዋን አሳርገው በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖሩት ። በዚያው ዓመት ሥጋዋ እስከ ነሐሴ 14 ቀን በገነት ከቆየ በኋላ ነሐሴ 14 ቀን መላእክት አምጥተው ለሐዋርያት ሰጡአቸውና በጌቴሴማኒ ቀበሩአት ፡ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ተነሥታ ፡ በክብርወደ ሰማይ ዐርጋለች ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት ፡ ትንሣኤና ዕርገት ይህንታምናለች። ታሳምናለች ። በየዓመቱም ነሐሴ 16 ቀን የፍልሰትዋን መታሰቢያ በታላቅ ሥነ ሥርዓት ታከብራለች (ስንክሳር ነሐሴ 16 ቀን) ።
ምዕራፍ ፰ ክብረ ቅዱሳን
ቅዱስ የሚለው ቃል በግእዝ ንጹሕ ክቡር ልዩ መሆንን የሚያመለክት ነው ። ይህ ቃል ለእግዚአብሔር የባሕርይ መግለጫ ነው ።እግዚአብሔር በባሕርዩ ቅዱስ ነውና ። ቅዱሳን የሚለውም ቃል በባሕርዩ ቅዱስ የሆነውን አምላክ ለሚያገለግሉ መላእክትና ደጋግ ሰዎች የሚሰጥነው ።
መላእክትን ቅዱሳን እንላቸዋለን ። ከማንኛውም ክፉ ነገር የራቁ ሥርዓታቸውን የጠበቁ ፡ እግዚአብሔርን ያወቁ ፡ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ስለሆኑ ቅዱሳን ይባላሉ ። ከመዐርገ መላእክት የደረሱ ደጋግ ሰዎችም በዚሁ የቅድስና ስም ይጠራሉ ። ራሱ ቅዱስ እግዚአብሔርም እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ··· ብሎአል ። (ዘሌዋ· 19፡2 1ጴጥ·1:15-16)
ነቢያት ፡ ሐዋርያት ጻድቃን ሰማዕታት ሁሉ ለቅዱስ እግዚአብሔርሲሉ ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድርገው ስለሰጡ ለስሙ ስለመሰከሩ ፡ በተጋድሎአቸውና በትሩፋታቸው ስላገለገሉ የቅድስናና የብፅዕና ማዕርግ ተሰጥቶአቸዋል ፡ ይሰጣቸዋልም ። ጌታችንም በወንጌል «አባት ሆይበእውነትህ ቀድሳቸው ቃልህ ቅዱስ ነው» ብሎ ስለቅድስናቸው ተናግሮአል ። (ዮሐ· 17፡17)። ከእነዚህ ሁሉ በላይ ግን ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም የቅዱሳን አክሊል የሆነች ቅድስት ናት ፡ ስለዚህም ቅድስተ ቅዱሳን ትባላለች።
ሀ)ክብረ መላእክት ቅዱሳን
ተፈጥሮአቸው
መላእክት በዕለተ እሑድ ከተፈጠሩ ፍጥረታት አንድ ክፍል ናቸው (ኩፋ· 2፡6-8) ። የመላእክት ተፈጥሮ ከእሳትና ከነፋስ እንደሆነ ቅዱስመጽሐፍ ያስረዳል ። (3መቃ· 2፡10-11)።መላእክት አንድ ጊዜ የተፈጠሩና በየጊዜው የማይባዙ ናቸው መላእክት በተፈጥሮአቸው ነባብያን ለባውያን ሕያዋን ኃያላንም ናቸው ።ሕማምና ሞት የለባቸውም ። የመላእክት ቁጥር በአኃዝ አይወሰንም ፡የብዙ ብዙ ናቸው ። መላእክት በነገድና በአለቃ ይከፈላሉ ፡ በነገድ መቶበከተማ ዐሥር እነደነበሩ ይታወቃል ።
አገልግሎታቸው
ቅዱሳን መላእክት ለእግዚአብሔር የቅርብ አገልጋዮች ናቸው ። ዘወትር በዙፋኑ ዙሪያ ሆነው ያመሰግኑታል (ራእ· 4፡8፡11)። በተልእኮአቸውም ፈጣኖች ናቸው (መዝ· 103፡4 ። ዕብ 1፡6)። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ለተልእኮ ይወርዳሉ ይወጣሉ ለሰው ልጆችም ይራዳሉ (ዮሐ·1፡52 ፡ ዕብ· 1፡14) ።
– የመላእክት ተልእኮ በጥቅሉ ሲገለጥ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል መላላክ ፡
– የሰውን ጸሎት ምጽዋትና መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ፡
– የእግዚአብሔርንም ምሕረትና ቸርነት ወደ ሰዎች ማድረስ ነው ። (ዳንኤል 9፡20–22 ። ሉቃ· 1፡13 ። የሐዋ· 10፡3-5) ።
– ሰዎች በሞቱ ጊዜ ነፍሶቻቸውን ወደ እግዚአብሔር ያቀርባሉ (ሉቃ· 16፡22 ። ሱቱ· ዕዝ· 6፡6-20)
– እያንዳንዱን ፍጥረት አዘውትረው ይጠብቃሉ (ማቴ· 18፡10 ። ዳን· 4፡13) ።
– ለምሕረትም ለመዓትም ይላካሉ (ሮሜ 9፡22) ።
-በመከራና በችግር ጊዜ ለተራዳኢነት ይላካሉ (የሐዋ· 12፡7-11፡ መዝ· 89፡7) ።
በፍጻሜ ዘመንም ይህ ዓለም በሚያልፍበት ጊዜ ይላካሉ ኃጥአንን ከጻጽቃን ይለያሉ (ማቴ· 24፡31 ። ራእ 7፤1-4)።
አማላጅነታቸው
የቅዱሳን መላእክት አማላጅነትና ተራዳኢነት የሰዎችን ጸሎትና ምጽዋት ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ በተሰጣቸው ባለሟልነት ነው።በቅዱስ መጽሐፍ በሰፊው እንደምንረዳው የብዙዎችን ሰዎች ጸሎት መሥዋዕትና ምጽዋት ወደ እግዚአብሔር እያቀረቡ የሚፈልጉትንመልካም ነገር ሁሉ ያሰጣሉ ። ደስታና የምሥራችን ሁሉ ለሰዎች ያበስራሉ ። ደስታን ማብሠር ፣ ማጽናናትና የምሥራችን መንገርከ እግዚአብሔር የተሰጣቸው ጸጋ ነው ። (ዘፍ· 48፡16 ፤ ዳን· 10፡10-12ሉቃ· 1፡13 ፡ ሉቃ· 1፡28-32 ፡ ይሁዳ 9) ።
የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት በቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ይነገራል ። በተለይ በሄኖክ ምዕራፍ 10፡7 እና በዘካርያስ 1፡12 ዘጸአ 23፡20-23፡ መዝ 33፡7 ላይ የተመለከቱት ጥቅሶች በግልጥ ያስረዳሉ።
ቅዱሳን መላእክት ንስሓ ገብተው በተመለሱ ሰዎች ደስታ እንደሚያደርጉ በሉቃስ ወንጌል 15፡10 ላይ የተጻፈው ስለ ሰው ልጆች ደኅንነትያላቸውን ፍቅርና አማላጅነት ያመለክታል ።
ክብራቸው
ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ ባለሟሎች ስለሆኑ ፡
– ለአምላካቸው ቀናእያን
– ለነፍሳት ቀዋምያን ስለሆኑ
– ለምሕረትም ለመዓትም ስለሚላኩ
– ሰዎችን በችግራቸው ጊዜ ስለሚረዱና ስለሚያማልዱ ቤተክርስቲያን ታከብራቸዋለች ። በስማቸው ጽላት ቀርፃ ፡ ቤተክርስቲያን አሳንፃድርሳናቸውን አስጽፋ እንዲመሰገኑና እንዲከበሩ ታደርጋለች ። የጸጋናየአክብሮት ስግደት ይሰገድላቸዋል ። (ዳንኤል 8፡15-18 ፡ ዘፍ· 22፡31።ዘኍል· 22፡31፡ ኢያሱ 5፡13-15)።
ለ) ቅዱሳን ነቢያት
ነቢያት በመንፈሰ እግዚአብሔር እየተቃኙ የወልደ እግዚአብሔርን ሰዉ መሆን እስከ ዳግም ምጽአቱ ተንብየዋል።ይህንንም በፈጸሙበት ጊዜ እስከ ሞት ድረስ ፀዋትወ መከራ የተቀበሉ አሉ። በዚህም መሠረት ቤተክርቲያናችን በቅድስናቸው ታከብራቸዋለች። ቅድስናቸውንም ትመሰክራለች።
የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን በደሙ ለማዳን እንደሚመጣ በትንቢትና በምሳሌ የተናገሩበትን የተስፋ ዘመን ለማስታወስ “ጾመ ነቢያት” በመባል በሚታወቀው ዘመነ ሱባዔ ከአዳም እስከ ክርስቶስ የተነሡ አበው ነቢያትን ታስታውሳቸዋለች።
ሐ) ቅዱሳን ሐዋርያት
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አብ እኔን እንደላከኝ እንዲሁ እኔ እልካችሁአለሁ ወደ ዓለም ሁሉ ሄዳችሁ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ አስተምሩ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ ···” ብሎ በላካቸው መሠረት ዓለምን ዙረው ያስተማሩና ስለክርስቶስ ስም የመሰከሩ ሐዋርያት ክርስቶስ የመረጣቸውና የቀደሳቸው ቅዱሳን ናቸው። በሐዋርያት እግር ተተክተው ስለ ስሙ የመሰከሩና የሚመሰክሩ ሁሉ የዚህክብርና ቅድስና ወራሾች ናቸው።
መ) ቅዱሳን ሰማዕታት
ስለ ክርስቶስ ስም በዓለውያን ነገሥታት ፊት እየቀረቡ ሳይፈሩና ሳያፍሩ የመሰከሩ በዚህም ምክንያት ሕይወታቸውን የሠዉ ሰማዕታት ቅዱሳን ናቸው።
ሠ) ጻድቃን
ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛና ቢነዳ በነፍሱ ግን ከተጐዳ ምንይጠቅመዋል? (ማቴ· 16፡26) ። ተብሎ በተጻፈው መሠረት ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር ሰጥተው ፣ ከዓለም ተለይተው ፣ በበዓት ተወስነው ፣ ግርማ ሌሊትን ድምፀ አራዊትን ፀብዐ አጋንንትን ታግሰው ፣ በምናኔ በተባሕትዎ በገድል በትሩፋት ዘመናቸውን ያሳለፉ ከክፉ ነገር የራቁ ፣ ጣዕመ ዓለምን የናቁ ፡ የሚታየውን በማይታየው ለውጠው የኖሩ ሁሉ የቅድስና መዓርግ አግኝተዋል ።
እነዚህን ስለ እግዚአብሔር ስምና ክብር የተጋደሉ ቅዱሳን ቅድስት ቤተክርስቲያን በዕድሜ በነገድ በፆታ ሳትለይ ለሁሉም በቀኖናዋመሠረት የቅድስና መዐርግ እየሰጠች ፡ ገድላቸውንና የሕይወታቸውን ታሪክ እየጻፈች ፣ ያደረጉትንና በየጊዜውም የሚያደርጉትን ተኣምራት እየመዘገበች በስማቸው ጽላት እየቀረፀች ፡ ቤተክርስቲያን እያሳነጸች ስማቸውና ክብራቸው የቅድስናም ታሪካቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ሲነገር እንዲኖር አድርጋለች ታደርጋለችም ።
የቅዱሳን ቃል ኪዳንና አማላጅነት፡
ቅዱሳን በዚህ ዓለም ሳሉ ባደረጉት ተጋድሎ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሙዋልነት ተሰጥቷቸዋል ። በዚህ ዓለም ሳሉ ሙታንን በማንሣት ፣ ድውያንን በመፈወስ ፣ አጋንንትን በማውጣት ብዙ የተአምርሥራ እንዲሠሩ መንፈሳዊ ኃይልና ሥልጣን እንደተሰጣቸው ሁሉ ከዚህዓለም በሞት በሚለዩበት ጊዜም ስማቸውን የሚጠራ መታሰቢያቸውን የሚያደርግ ፣ በአማላጅነታቸው የሚያምን ሁሉ ዋጋ እንደሚያገኝ ከልዑል እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተሰጥቶአቸዋል። ጻድቁን በጻድቅ ፣ነ ቢዩን በነቢይ ስም የተቀበለ በክርስቶስ ተከታዮችና አገልጋዮች ስምቀዝቃዛ ውሃ እንኳ የሰጠ ዋጋው እንደማይጠፋበት ጌታችን በወንጌል አረጋግጦአል ። (ማቴ 10፡41-42)።
ቅዱሳን በዐፀደ ሥጋ ብቻ ሳይሆን በዐፀደ ነፍስም ያማልዳሉ፡ ለዚህም ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ (ዘጸአ 32፡2-15 ፣ ሄኖክ 12፡33-40) በነፍስ ሕያዋን ናቸውና (ሉቃ 20፡37-40)።
የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነው ፣ በሕያዋንም ላይ ሲሠራ ይኖራል ፣ ቃል ኪዳኑም አይለወጥም ፣ ቅዱሳኑም ሕያዋን እንደሆኑ ራሱ ተናግሯል። በዚህ እምነትና ትምህርት መሠረት ቤተክርስቲያን የቅዱሳን ሐዋርያትን የሰማዕታትንና የጻድቃንን ቃል ኪዳንና ክብር ትቀበላለች።
ስለ ክርስቶስ ስምና ክብር ሁሉን ትተው የተከተሉት ! በተጋድሎአቸውም መስቀሉን ተሸክመው በመከራው የመሰሉት ቅዱሳን በተሰጣቸው ቃል ኪዳን በዚህ ዓለም ሳሉ ብቻ ሳይሆን ክርስቶስ ዳግመኛ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ በ12 የፍርድ ዙፋን ተቀምጠው በእስራኤል ዘነፍስ እንደሚፈርዱ ቃል ኪዳን ተሰጥቶአቸዋል ። (ማቴ·19፡28)።
ቅዱሳንን ከአምላካቸው በተሰጣቸው ቃል ኪዳን መሠረት ቤተክርስቲያን ታከብራቸዋለች ። ምእመናን ይማጸኑባቸዋል ። ቤተክርስቲያን በስማቸው እየሠሩ መታሰቢያቸውን እያደረጉ ፣ ሥዕላቸውን እየሣሉ የቅድስና ሕይወታቸውን ሲያስታውሱ ይኖራሉ።
ረ) ክብረ ዐዕመ ቅዱሳን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በገድላቸውና በትሩፋታቸው ፡ እግዚአብሔርን አገልግለው ስለ ስሙና ስለ አምልኮቱ መስክረው በሞት የተለዩ ቅዱሳንን ዐፅም ታከብራለች።
በሕይወት ሳሉ በትምህርታቸውና በጸሎታቸው ፡ ከሞትም በኋላ በመቃብራቸው ወይም በዐፅማቸው ላይ የተለያየ ምልክት የታየላቸው ቅዱሳን ዐፅማቸው ከቤተ ክርስቲያን ቅፅር ግቢ በልዩ ቦታ በክብር እንዲቀመጥ ይደረጋል።
የጥንት ክርስቲያኖች በስደት ጊዜ ከቦታ ወደ ቦታ ሲዘዋወሩና በግበበ ምድር ሲኖሩ የቅዱሳን ሐዋርያትንና የሰማዕታትን ዐፅም በክብር ጠብቀው ይኖሩ ነበር ። እግዚአብሔርም በቅዱሳኑ ዐፅም አማካኝነት ተአምራትን ያሳያል በረከትንና ልዩ ልዩ ፈውስን ይሰጣል ።(2 ነገሥ ·13፡20-21)።
ለቅዱሳን ዐፅም ክብር መስጠት ፡ በክብር ማስቀመጥና መጠበቅ መጽሐፋዊ መሠረት አለው። እስራኤላውያን የያዕቆብንና የዮሴፍን ዐፅም ከግብጽ በክብር አውጥተው በክብር ቦታ አኑረውታል ። (ዘጸአ· 13፡19፤ኢያሱ 24፡32 የሐዋ· 7፡15)። ከአዳም እስከ ኖኅ የነበሩ አበውም ዐፅማቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ በክብር ተጠብቆ ይኖር እንደነበርና በማየ አይኅ ጊዜም ኖኅ በመርከብ ውስጥ ይዞት እንደገባ የታሪክ ትውፊት ያስረዳል ።
ነፍሳቸው በገነት ያለች ቅዱሳንን ካከበርን ከነፍሳቸው ጋር መከራ የተቀበለና የተሠቃየ ሥጋቸውንና ዐፅማቸውንም ልናከብር ይገባል። (ፍት· ነገ· አን· 20)።
እግዚአብሔር የቅዱሳንን ዐፅም ለፈውስና ለተለያየ ጸጋ ምልክትስለሚያደርገው ቤተክርስቲያናቸን ታከብረዋለች ። ልዩ የክብር ቦታምትሰጠዋለች ። (መዝ· 33፡19-20)።
ቅዱሳን ደማቸው በፈሰሰበት ዐፅማቸው በተከሰከሰበት ገድላቸው በተፈጸመበት ፡ ወዛቸው በነጠበበት ፡ ቤተክርስቲያናቸው በታነጸበት ፡ ስማቸው በተጠራበት ሁሉ ተአምራት ሲያደርጉ ይኖራሉ የክብራቸውና የቅድስናቸው ምልክትም ይህ ነው ። የቅዱስ እግዚአብሔር ምስክሮች ናቸውና። (መዝ· 33፡20 ። ሉቃ· 24፡47)
ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል ሁለት ፍች አለው። አንደኛው በክርስቶስ አምነው የተጠመቁ የምእመናን አንድነት ወይም ማኅበረ ምእመናን ነው። (ፍት· ነገ· አን 1፡ ማቴ· 18፡17 ፡ የሐዋ· 20 ፡28) በብሉይኪዳን የነበሩ ሕዝበ እግዚአብሔር ቤተ እሥራኤል ተብለው ይጠሩ እንደነበሩ በሐዲስ ኪዳን ያሉ ሕዝበ እግዚአብሔርም ቤተክርስቲያን ተብለዋል ። ይህም ሕዝበ ክርስቲያን ነገደ ክርስቲያን ማለት ነው።
ሁለተኛው አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምበት ምእመናን የሚሰበሰቡበት ሕንፃ ቤተክርስቲያን ነው።
ሐመረ ኖኅ ፡ ሐይመተ አብርሃም ደብተራ ኦሪትና መቅደሰ ሰሎሞን ለቤተክርስቲያን ምሳሌዎች ሆነው መሥዋዕት ሲሠዋባቸው አምልኮተእግዚአብሔር ሲፈጸምባቸውና ስመ እግዚአብሔር ሲቀደስባቸው ኖረዋል።
እነዚህ ሁሉ ካለፉ በኋላ የቤተክርስቲያን መሠረትና ራስ የሆነውጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊት ቤተ ክርስቲያንን በደሙ መሠረተ።
የቤተክርስቲያን አባቶች በጸሎተ ሃይማኖት ውስጥ በወሰኑት መሠረት ፡ «ቤተክርስቲያን አንዲት ቅድስት በሁሉ ዘንድ ያለችሐዋርያት የሰበሰቡአት» ትባላለች (ጸሎተ ሃይማኖት)
ቤተክርስቲያን ፦
– ማኅደረ እግዚአብሔር ናት ፡
– የትምህርት የጸሎትና የአምልኮት ቤት ናት ፡ (ማቴ 21፡13 ፣ ዮሐ 2፡7 ፤ መዝ 68፡9)።
– የኃጢአት ማስተሥርያ መስገጃና መማጸኛ ናት ፡
– ወንጌል ይሰበክባታል ፡ ቅ/ቁርባን ይቀርብባታል ፡ በጥምቀት ልጅነት ይሰጥባታል ።
– የክርስቲያኖች ዐዕም ያርፍባታል ፤
– በሰዎች መካከል የዕድሜ ፡ የነገድ የጾታ ልዩነት ሳይደረግ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጥባታል ።
– ቤተክርስቲያንን ቤተክርስቲያን የሚያሰኛትና ከሌላው ቤት ልዩ የሚያደርጋት ፦
- በኤጲስ ቆጶሳት (ጳጳሳት) ጸሎትና ቡራኬ ትቀደሳለች፡
- በቅብዐ ሜሮን ትከብራለች፡
- ታቦተ ሕግ ይቀመጥባታል፡
- ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ሁሉ : ይፈጸሙባታል።
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት የቤተክርስቲያን የሕንፃ አሠራር የተለያየ ሆኖ በመሠረተ አቅዋም ሦስት ክፍል አለው፡
ሀ) ቅኔ ማሕሌት ፦ መዘምራን ስብሓተ እግዚአብሔር ማሕሌተ እግዚአብሔር የሚያደርሱበት ክፍል ነው።
ለ) ቅድስት ፦ የቤተክርስቲያኑ ማዕከላዊ ክፍል ነው ፣ ምእመናንም ሥጋውንና ደሙን የሚቀበሉበት በዚሁ ነው ።ሐ) መቅደስ ፦ ታቦተ ሕጉ የሚቀመጥበት መንበር ያለበት ሥጋውና ደሙ የሚፈተትበት ባጠቃላይ ሥርዓተ ቅዳሴው የሚፈጸምበት ዋና ክፍል ነው። በዚህ ክፍል መግባት የሚችሉ ሥልጣነ ክህነት ያላቸው ብቻ ናቸው ።
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ቤተ መቅደሱ ሦስት ዋና በሮች አሉት።
ምዕራብ፡ ስብሓተ እግዚአብሔር ይደርስበታል ሥጋውና ደሙ ይሰጥበታል።
ሰሜን፡ ወንዶች ምእመናን ያስቀድሱበታል ካህናት ሰዓታት ያደርሱበታል ።
ደቡብ፡ ምእመናት ሴቶች ያስቀድሱበታል ይጸልዩበታል ።
በቤተክርስቲያን ጉልላት ላይ መስቀል ይደረጋል የቤተክርስቲያን አርማ መስቀል ነውና። የመስቀል ምልክት ከሌለው ቤተክርስቲያን አይባልም። በቤተክርስቲያን በስተምሥራቅ ቤተልሔም በስተምዕራብ ደጀ ሰላም ይገኛል። ሁሉም የተለያየ አገልግሎት አላቸው።
ምዕራፍ ፱ ቤተክርስቲያን
ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል ሁለት ፍች አለው። አንደኛው በክርስቶስ አምነው የተጠመቁ የምእመናን አንድነት ወይም ማኅበረ ምእመናን ነው። (ፍት· ነገ· አን 1፡ ማቴ· 18፡17 ፡ የሐዋ· 20 ፡28) በብሉይኪዳን የነበሩ ሕዝበ እግዚአብሔር ቤተ እሥራኤል ተብለው ይጠሩ እንደነበሩ በሐዲስ ኪዳን ያሉ ሕዝበ እግዚአብሔርም ቤተክርስቲያን ተብለዋል ። ይህም ሕዝበ ክርስቲያን ነገደ ክርስቲያን ማለት ነው።
ሁለተኛው አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምበት ምእመናን የሚሰበሰቡበት ሕንፃ ቤተክርስቲያን ነው።
ሐመረ ኖኅ ፡ ሐይመተ አብርሃም ደብተራ ኦሪትና መቅደሰ ሰሎሞን ለቤተክርስቲያን ምሳሌዎች ሆነው መሥዋዕት ሲሠዋባቸው አምልኮተእግዚአብሔር ሲፈጸምባቸውና ስመ እግዚአብሔር ሲቀደስባቸው ኖረዋል።
እነዚህ ሁሉ ካለፉ በኋላ የቤተክርስቲያን መሠረትና ራስ የሆነውጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊት ቤተ ክርስቲያንን በደሙ መሠረተ።
የቤተክርስቲያን አባቶች በጸሎተ ሃይማኖት ውስጥ በወሰኑት መሠረት ፡ «ቤተክርስቲያን አንዲት ቅድስት በሁሉ ዘንድ ያለችሐዋርያት የሰበሰቡአት» ትባላለች (ጸሎተ ሃይማኖት)
ቤተክርስቲያን ፦
– ማኅደረ እግዚአብሔር ናት ፡
– የትምህርት የጸሎትና የአምልኮት ቤት ናት ፡ (ማቴ 21፡13 ፣ ዮሐ 2፡7 ፤ መዝ 68፡9)።
– የኃጢአት ማስተሥርያ መስገጃና መማጸኛ ናት ፡
– ወንጌል ይሰበክባታል ፡ ቅ/ቁርባን ይቀርብባታል ፡ በጥምቀት ልጅነት ይሰጥባታል ።
– የክርስቲያኖች ዐዕም ያርፍባታል ፤
– በሰዎች መካከል የዕድሜ ፡ የነገድ የጾታ ልዩነት ሳይደረግ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጥባታል ።
– ቤተክርስቲያንን ቤተክርስቲያን የሚያሰኛትና ከሌላው ቤት ልዩ የሚያደርጋት ፦
- በኤጲስ ቆጶሳት (ጳጳሳት) ጸሎትና ቡራኬ ትቀደሳለች፡
- በቅብዐ ሜሮን ትከብራለች፡
- ታቦተ ሕግ ይቀመጥባታል፡
- ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ሁሉ : ይፈጸሙባታል።
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት የቤተክርስቲያን የሕንፃ አሠራር የተለያየ ሆኖ በመሠረተ አቅዋም ሦስት ክፍል አለው፡
ሀ) ቅኔ ማሕሌት ፦ መዘምራን ስብሓተ እግዚአብሔር ማሕሌተ እግዚአብሔር የሚያደርሱበት ክፍል ነው።
ለ) ቅድስት ፦ የቤተክርስቲያኑ ማዕከላዊ ክፍል ነው ፣ ምእመናንም ሥጋውንና ደሙን የሚቀበሉበት በዚሁ ነው ።ሐ) መቅደስ ፦ ታቦተ ሕጉ የሚቀመጥበት መንበር ያለበት ሥጋውና ደሙ የሚፈተትበት ባጠቃላይ ሥርዓተ ቅዳሴው የሚፈጸምበት ዋና ክፍል ነው። በዚህ ክፍል መግባት የሚችሉ ሥልጣነ ክህነት ያላቸው ብቻ ናቸው ።
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ቤተ መቅደሱ ሦስት ዋና በሮች አሉት።
ምዕራብ፡ ስብሓተ እግዚአብሔር ይደርስበታል ሥጋውና ደሙ ይሰጥበታል።
ሰሜን፡ ወንዶች ምእመናን ያስቀድሱበታል ካህናት ሰዓታት ያደርሱበታል ።
ደቡብ፡ ምእመናት ሴቶች ያስቀድሱበታል ይጸልዩበታል ።
በቤተክርስቲያን ጉልላት ላይ መስቀል ይደረጋል የቤተክርስቲያን አርማ መስቀል ነውና። የመስቀል ምልክት ከሌለው ቤተክርስቲያን አይባልም። በቤተክርስቲያን በስተምሥራቅ ቤተልሔም በስተምዕራብ ደጀ ሰላም ይገኛል። ሁሉም የተለያየ አገልግሎት አላቸው።
ምዕራፍ ፲ ታቦት
ታቦት እግዚአብሔር በደብረ ሲና ዐሠርቱ ቃላትን በላዩ ጽፎ ለሙሴ ለሰጠው ጽላት ማደሪያ ፡ ማኖሪያ ነው ። በቤተክርስቲያናችን ግን ጽላቱ ታቦት እየተባለ ይጠራል። ይህም አዳሪውን በማደሪያው ለመጥራት ነው ። ታቦቱ የጽላቱ ማደሪያ ማኖሪያ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር መገለጫ ነው ። በታቦት ፊት የሚጸለየው ፡ የሚሰገደው ዐሠርቱ ቃላት ስለተጻፉበት ብቻ አይደለም እሥራኤል ኃጢአት ሠርተው ሲበድሉ ፡ ሲያሳዝኑትና ሲያስቀይሙት ፡ ተመልሰው ንስሓ ገብተው ሲያለቅሱና ሲለምኑት እግዚአብሔር እየራራ በቃል ኪዳን ታቦቱ እየተገለጠ ይመራቸውና ያነጋግራቸው ስለነበረ ታቦት የምህረትና የደኅንነት መግለጫም በመሆኑ ነው። (ዘፀ· 25፡20–25)።
የታቦት አገልግሎት በብሉይ ኪዳን ተጀምሮ የቀረ አይደለም። ጽላተ ሙሴ ወደ አትዮጵያ ስለመጣች ሀገራችን ኢትዮጵያ ከክርስትና በፊት ብሉይ ኪዳንን ተቀብላ አምልኮተ እግዚአብሔርን አጽንታ ቆይታለች ። የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብሉይ ኪዳንንና ሥርዓቱን ተቀብላ በመጠበቅ ብቻ ያቆየችው አይደለም ፣ በወንጌል “ኦሪትንና ነቢያትን ልፈጽማቸው እንጂ ልሽራቸው አልጣሁም ። እውነት እውነት እላችኋለሁ ሥራዋ አንዲት ፡ አቀራረጻ አንዲት የምትሆን የውጣ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ሁሉም እስኪሆን ፡ እስኪደረግ ድረስ ከኦሪት ከነቢያት ተለይታ አታልፍም ከነዚህ ትእዛዛት እንዲቱን አሳንሶ የሻረ ፣ ለሰው እንዲህ ታንሳለች ብሎ የሚያስተምርበ መንግሥተ ሰማይ ታናሽ ይሆናል ። እንዲህ የሚሠራ የሚያስተምር ግን እርሱ በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይሆናል” ። (ማቴ· 5፤17-19) ብሎ ባስተማረው መሠረት ቤተክርስቲያን ከብሉይ ኪዳን ወስዳ ከምትገለገልባቸው አንዱ ስመ እግዚአብሔር የተጻፈበት ጽላተ ኪዳን (ታቦት) ነው። ታቦት ፡ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ጸንቶ ለሚኖረው ቃል ኪዳን ሕያው ቃሉ የተጻፈበት የኪዳን ምስክር ነው ። ጥንታዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ኦሪትን ከሥርዓተ ወንጌል አጣምራ የያዘች ስለሆነ በክርስትና ጊዜ ከብሉይ ኪዳን ያገኘቻቸውን በክርስትና መንፈስ እየተረጐመች ትገለገልባቸዋለች።
እሥራኤል ታቦተ ኪዳኑን እየያዙ በተጓዙባቸው መንገዶችና በሠፈሩባቸው መንደሮች ሁሉ ብዙ የተአምራት ሥራ ተሠርቶላቸዋል ። ጽላተ ሕጉን ይዘው በዘመቱባቸው የጦር መስኮች ሁል ድል አድርገውበታል ። ኃጢአት በሠሩ ጊዜ ረድኤተ እግዚአብሔር እየተነሣቸው ድል ይሆኑ ነበር ። (ሳሙ· 4፡1) በሀገራችንም ታቦት ኃይለ መዊእና ኃይለረድኤት ያለው በመሆኑ ቤተክርስቲናችን የውጭ ጠላት በተነሣ ጊዜ ሁሉ ታቦቷን እየያዘች በግንባር ቀደምትነት በመሰለፍ ድል ስታደርግበትና ሀገሯን ስትጠብቅበት ኖራለች። በታቦተ ሕጉ አምነው የተቀበሉት፡ያከበሩት ሁሉ የተአምራቱ በረከት ሲደርሳቸው የተዳፈሩትና ሳይገባቸው የነኩት ደግሞ ተቀስፈውበታል ። ጠፍተውበታልም። (1ሳሙ· ምዕ· 4፡4-6 ። 2ሳሙ· ምዕ·6)። ታቦት በሐዲስ ኪዳንም በቤተክርስቲያናችን አምልኮተ እግዚአ ብሔር ይፈጸምበታል። ታቦት እውነተኛው የሕይወት ምግብ የክርስቶስ ሥጋና ደም የሚቀርብበትና የሚፈተትበት መሠዊያ ነው። የሚከበረውና የሚሰገድለትም ስለዚህ ነው ።
ቅዱስ ጳውሎስ “ክርስቶስን ከሰይጣን ጋር አንድ የሚያደርገውማነው? ምእመናንንስ ከመናፍቃን ጋር አንድ የሚያደርጋቸው ማነው? የእግዚአብሔርንስ ታቦት በጣዖት ቤት ውስጥ የሚያኖር ማነው?” በማለት አስተምሮአል ። (2 ቆሮ 6፡15-16)።
ከዚህም በላይ ወንጌላዊ ዮሐንስ “ከዚህ በኋላ በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ በመቅደሱም ውስጥ የእግዚአብሔርየሕጉ ታቦት ታየ” በማለት በራእዩ ገልጾአል ። (ራእ 11፡19)።
ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከብሉይ ኪዳን የተቀበለችውን ታቦተ ሕግ አክብራ በራሷ እየተሸከመች አምልኮተ እግዚአብሔርን ስትፈጽም ፡ ስለእግዚአብሔር ስም በአደባባይ ስትመሰክር ትኖራለች ። ታቦት ለቤተክርስቲያናችን ትልቁ የእምነቷና የሥርዓቷ መግለጫ ነው ። ታቦት በስመ ሥላሴ ፡ በቅድስት ድንግል እመቤታችን ፡ በቅዱሳን መላእክት በነቢያት ፡ በሐዋርያት ፡ በጻድቃንና ሰማዕታት ስም ይቀረጻል ። ታቦት በማይገባቸው ሰዎች ቢገሠሥ ቢማረክ እንደገና በኤጲስ ቆጶስ ጸሎት ተባርኮ ይቀደሳል ፡ ሜሮን ተቀብቶይከበራል ።
– ሙሴ እንደ መጀመሪያዎቹ ጽላት እንደገና እንዲቀርጽ በታዘዘው መሠረት ጽላት በየጊዜው ይቀረጻል ፡ (ዘፀ 34 ፡ 1) ።
– ታቦት ስመ እግዚአብሔር ስለ ተጻፈበት ይሰገድለታል (ፊል2፡ 10)።
– እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ታቦት ከማይነቅዝ ዕፅና ከዕብነበረድ ይቀረጻል ።– በታቦቱ ላይ ስመ እግዚአብሔር በ4 ገጽ ይጻፍበታል ።
– ሥዕለ ኪሩብ ሥዕለ ሥላሴ ሥዕለ ቅ/ድንግል ማርያም ሥዕለ ዮሐንስ ወንጌላዊ ይሣልበታል ።
– በኤጴስ ቆጶስ ጸሎት ተባርኮ ይቀደሳል ፡ ሜሮን ተቀብቶ ይከብራል ፡ ከዚያም በመንበሩ ይሰየማል ።
– ጽላት በሌለበት ቤተክርስቲያን ቅዳሴ አይቀደስም ። ቤተክርስቲያንም አይባልም ።
– ታቦቱን ለመያዝና ለመሸከም ሥልጣን ያላቸው ጳጳሳትና ቀሳውስት ናቸው ።
ምዕራፍ ፲፩ ሃይማኖትና ምግባር
ሃይማኖትና ምግባር ሁለቱ በአንድነት በክርስትና ሕይወት ውስጥ ሲገኙ ደኅንነትን እንደሚያሰጡ ቤተክርስቲያናችን ታምናለች ታስተምራለችም ። ነገር ግን እምነት ይቀድማል ፣ መልካም ሥራ ይከተላል ።
ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደገለጠው «እምነት መሠረት ናት ፤ ሌሎቹ ግን ሕንፃና ግንብ ናቸው » ይኸው አባት ይህን ሲያብራራ እንዲህ ይላል «መሠረት ሕንፃውን ሁሉ እንደሚሸከም እምነትም ምግባራትን ሁሉ ትይዛለች ማለት ምግባር ታሠራለች ። ሕንፃ ያለ መሠረት ሊቆምና ሊታይ እንደማይችል ክርስቲያንም ያለ ምግባር ክርስቲያን መሆን አይችልም» ብሎአል ። (ዮሐ· አፈወርቅ ድርሳን 9)።
ሃይማኖት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያረጋግጥ ፣ የማናየውንምነገር የሚያስረዳ ነው ። ለአባቶች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና ። (ዕብ11፡12)። ሃይማኖት የማይታየውን እንደሚታይ አድርጎ ሊያረጋግጥና ሊያስረዳ የሚችለው በምግባር ሲገለጥና ሲጸና ነው ።
ቅዱስ ጳውሎስ «ሃይማኖት ፣ ተስፋ ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ ፡ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው» በማለት ለምግባር ከፍተኛ ደረጃ ሰጥቶአል ። (1 ቆሮ· 13፡13)።
ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም እምነትና ምግባር በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ መነጣጠል እንደሌለባቸው ሲገልጥ ሥራ የሌለው ሃይማኖት አይጠቅምም ፣ አያድንም ፣ እምነት ፍጹምና ሕያው ሊሆን የሚችለው በሥራ ነው። ሃይማኖትና ምግባር የሌሉት ሰው ከንቱ ነው ፤ ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየሃይማኖት የሞተ ነው ካለ በኋላ የአብርሃምና የረሀብን እምነትና ምግባር ምሳሌ አድርጎ አቅርቦአል ። (ያዕ· 2፡14-26)። በዚህ መሠረት መልካም ሥራ የሃይማኖት ውጤት ወይም ፍሬ ነው እውነተኛ ሃይማኖት ያለው ሁሉ ግድ መልካም ሥራ ይሠራል ። (1 ቆሮ· 13:2)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም «መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ይቆረጣል ፣ ወደ እሳትም ይጣላል» (ማቴ 7፡19)። ካለ በኋላ «በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ፡ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም» ብሎ መዳን ወይም መንግሥተ ሰማያት መግባት የሚቻለው ምግባር በሃይማኖት መሠረትነት ላይ ሲጸና ሃይማኖትም በምግባር ሲገለጥና ሲፈጸም መሆኑን ተናግሮአል።(ማቴ· 7፡20-21 ፤ ሉቃ 3፡8)።
በፍርድ ቀን ማንም ሰው የሚጠየቀው አምኖ ስለሠራው ሥራ ነው እንጂ ምግባር ስለሌለው ሃይማኖቱ አይደለም (ማቴ· 25፡41-45)። በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የተነገረው ሁሉም እንደየሥራው ዋጋውን ይቀበላል የሚል ነው ። (ማቴ· 16፡27 ፣ ዮሐ 5፡28-29 ፣ 2 ቆሮ 5፡10 ፣ ራእ· 14፡13 ፣ 20፡12 እና 22፡12)።
በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንሃይማኖት ብቻውን እንደማይጠቅም አውቃ በሃይማኖት ላይ ምግባር መሥራት እንደሚገባ ታምናለች ታስተምራለች ።
ክፍል ፪: ሥርዓተ አምልኮት
ጾም ሰውነት ከሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ መከልከልና የጾም ጊዜ እስኪፈጸም ድረስ ከጥሉላት ፡ በዚህም በጾሙ ጊዜ ለተወሰነ ሰዓት ከማንኛውም ምግብ ተከልክሎ መጾም ነው ። (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 15 ፡ ማቴ· 6፡16)። በጠቅላላም ለሰውነት የሚያምረውን የሚያስጐመጀውን ነገር ሁሉ መተው ነው ።
የጾም ዋና ዓላማም ፈቃደ ሥጋ ለፈቃደ ነፍስ እንዲታዘዝ ለማድረግና በደልን ለማስተሥረይ የነፍስ ዋጋን ለማብዛት ነው ።
ጾም ከሃይማኖት ጋራ ግንኙነት ስላለው የአፈጻጸሙ ሥርዓት ይለያይ እንጂ ሃይማኖት ላለው ሁሉ ጾም አለው ። ይልቁንም በብሉይ ኪዳን ጾም ከፍተኛ ቦታ ነበረው ። የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ጋር በሚገናኙበት ወራት እህል ውሃ ባፋቸው አይገባም ነበር ። (ዘፀ· 34፡28)። በኃጢአት ብዛት የታዘዘው የእግዘአብሔር መዓት የሚመለሰው ሕዝቡ በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር ። (ዮናስ 3:7–100 ፡ ኢዩ· 2:12–18) ።
በሐዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌ የሥራ መጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው ” (ማቴ· 4፡2 ፣ ሉቃ· 4፡2)። ጾም ርኩሳን መናፍስትን የማራቅ ኃይል እንዳለው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮአል (ማቴ· 17፡21 ፡ ማር· 9፡2)። ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የታዘዙ ሐዋርያትም ከመንፈስ ቅዱስ በየጊዜው ትእዛዝ የሚቀበሉት በጾምና በጸሎት ላይ እንዳሉ ነበር ። (የሐዋ· ሥራ 13፡2)።
ለስብከተ ወንጌል የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ቀሳውስት የሚሾሙትም በጾምና በጸሎት ነው ። (የሐዋ· ሥራ 13፡3 ፣14፡23)።
ደጋግ ሰዎች ሁሉ የፈለጉትን ያዩና ያገኙ በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን ማልደው ነው ። (ዕዝራ 8፡21 ፡ ነህምያ 9፡1–3 ፡ አስቴር 4፡16–17 ፣ የሐዋ· ሥራ 10፡30 ፡ 13፡2–3)።
የጾም ሃይማኖታዊ ትርጉም ፈጣሪን መለመኛ የኃጢአት ማስተሥረያ ስለሆነ በጾም ወራት ላምሮት ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኃይል ተቃራኒ የሆነ ሥጋዊ ፍትወትን ከሚያበረታቱ ከአልኮል መጠጥ ፣ ከሥጋና ከቅቤ ፣ ከወተትና ከእንቁላል መከልከል ይገባል። (ዳን 10፡2–3)። ጾም በትምህርተ ሐዋርያትና በሊቃውንትም ዘንድ ሲሰበክ ኖሯል። (ፍትሕ‧መን‧አን 15 ፡ ዲድስቅልያ አን‧ 29)።
ነዳያንን ለመመገብ የሚጾም ንዑድ ክቡር ነው እንደተባለ ጦመኛው ለምሳው ወይም ለራቱ ያሰበውን ወጭ ነዳያንን እንዲረዳበት ለድኩማን ድርጅት ወይም በቤተክርስቲያን አካባቢ ለሚገኙ ነዳያን መስጠት ጾሙን የበለጠ ፍጹም ያደርገዋል ። (ኢሳ‧ 58:6–11)።
ጾም ከመባልዕት መከልከል ብቻ ሳይሆን ዐይን ክፉ ከማየት ፣ አንደበት ክፉ ከመናገር ፣ ጆሮ ክፉ ከመስማት የተቆጠበ እንደሆነ ጾሙን እውነተኛ ጾም ያደርገዋል ። (ማቴ‧ 5፡21–30)። (ያሬድ ጾመ ድጓ)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የራስዋ የሆነ የጾም ሕግና ሥርዓት አላት፡
በሕጓም መሠረት ሰባት አጽዋማት አሉአት ፡
1ኛ. ዐቢይ ጾም
2ኛ. ረቡዕና ዓርብ
3ኛ. ነነዌ
4ኛ. ገሃድ
5ኛ. ጾመ ነቢያት
6ኛ. ጾመ ሐዋርያት
7ኛ. ጾመ ፍልስታ ለማርያም
ሀ) ዐቢይ ጾም
ዐቢይ ጾም :- ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የዓርባ ቀናት ጾም ነው። (ማቴ 4:1) ቤተ ክርስቲያንም ጌታ ያደረገውን ምሳሌ ተከትላ ትጸማለች
ዐቢይ ጾም ስምንት ሳምንታት ወይም 55 ቀኖች አሉት ። የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል ይባላል ። ሕርቃል (ኢራቅ ሊዮስ) የቤዛንታይን ንጉሥ ነበር ፣ (614 ዓ.ም)። ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበትም ምክንያት እንደሚከተለው ነው ። በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር ። እሱ ወደ ፋርስ ዘምቶ እነርሱን ድል አድርጎ መስቀሉን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል ። በዚህ ምክንያት ክርስቲያኖች ተደስተው ለስሙ መታሰቢያ ይህን የጾም ሳምንት በቀኖና ውስጥ አስገብተውለታል ቤተ ክርስቲያናችንም በቀኖናዋ አስገብታ ተቀብላዋለች ከዐቢይ ጾምም ጋር አንድ ሁኖ ተቆጥሮአል ። (ፍት· ነገ· 15)።
የመጨረሻው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ነው ፡ ሐዋርያት የጌታችንን ነገረ መስቀል እያሰቡ የጾሙት ነው ። ያም ሆነ ይህ ሁሉም ከዐቢያ ጾም ጋር አንድ ሆነው ተቆጥረዋል ።
ዐቢይ ጾም መባሉ
1ኛ የጌታ ጾም ስለሆነ ፡
2ኛ የሰይጣን ፈተናዎች (አርእስተ ኀጣውእ) ድል የተነሱበትናየሚነሱበት በመሆኑ ነው፡
የቤተ ክርስቲያናችንን መዝሙር ንባቡን ከዜማው አስማምቶና አጠናቅሮ የተናገረው አትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በጾመድጓው በዓቢይ ጾም ለሚገኙት እሑዶች ሁሉ የተለየ መዝሙር ስለሠራላቸው እያንዳንዱ እሑድ በመዝሙሩ ስም ይጠራል ።
የመጀመሪያው እሑድ ዘወረደ ይባላል
በመጽሐፉ መጀመሪያ አምላክ ከሰማይ መውረዱን ሰው መሆኑንና መሰቀሉን ስለሚያወሳ ነው። (ዮሐ· 3፡13)።
ሁለተኛው እሑድ ቅድስት ይባላል
በተለይ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ስለሚያወሳ ነው ።
ሦስተኛው እሑድ ምኩራብ ነው
ጌታ በመዋዕለ ትምህርቱ በሰንበት በምኩራብ ገብቶ ማስተማሩን ስለሚያወሳ ነው።
አራተኛው እሑድ መጻጉዕ ነው
ድውያንን መፈወሱን ዕውራንን ማብራቱን የሚያነሣ መዝሙር ይዘመርበታል ። (ዮሐ· 5፡1–9)።
አምስተኛው እሑድ ደብረ ዘይት ይባላል
በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሁኖ ያስተማረውን የዳግም ምጽአት ነገር የሚያስታውስ መዝሙር ይዘመራል ።
ስድስተኛው እሑድ ገብር ኄር ነው
የጌታውን ብር ተቀብሎ ያተረፈው ፡ በጌታውም ፊት ምስጋናን ያገኘው ሰው ታሪክ ይነገርበታል ፡ ይዘመርበታል ።
ሰባተኛው እሑድ ኒቆዲሞስ ነው
በሌሊት ወደጌታ እየመጣ ይማር የነበረውን የኒቆዲሞስን ታሪክየ ሚያስታውስ መዝሙር ይዘመርበታል ።
ስምንተኛው እሑድ ሆሣዕና ነው
ጌታ ሆሣዕና በአርያም እየተባለ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት ዕለት መታሰቢያ ነው። ከሠርከ ሆሣዕና እስከ ትንሣኤ ያለው ሰባት ቀን «ሰሙነ ሕማማት» ይባላል ። በነዚህ ቀናት ብዙ አዝማደ መባልዕት አይበሉም ። ስግደት ይሰገዳል ። የጌታን መከራና ሞት የሚያስታዉሱ ምንባባት ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከድርሳናት ተውጣጥተው በግብረ ሕማማት ይነበባሉ ። አዳም ከፈጣሪው ተጣልቶ የኖረውን የጨለማና የመከራ ዘመን በማስታወስ መንበረ ታቦቱ በጥቍር ልብስ ይሸፈናል ። ልብሰ ተክህኖውም ጥቋቁር ነው ። ይህ ሳምንት የ5500 ዘመን ዓመተ ፍዳና ዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ስለሆነ በዚህ ሳምንት ጸሎተ ፍትሐትና ጸሎተ አስተሥርዮ አይፈጸምም ። ጸሎተፍት ሐትና ጸሎተ አስተሥርዮ የሚደረገው የሆሣዕና ዕለት ነው ።
ጸሎተ ሐሙስ :-
ጸሎተ ሐሙስ ጌታ በፍጹም ትሕትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበትና ግብር ያገባበት ፡ ምሥጢረ ቁርባንን ያሳየበት ዕለት ነው። በዚህ ዕለት ቅዳሴ ይቀደሳል ። ከቅዳሴውም ቀደም ብሎ ካህኑ ውኀውን በብርት አድርጎ ጸሎተ አኰቴት አድርሶ በጌታ አምሳል የምእመናንን እግር ያጥባል ጸሎተ ቅዳሴውም ከተፈጸመ በኋላ ምእመናኑ ወደየቤታቸው ይሄዳሉ ።
ከጸሎተ ሐሙስ በበነጋው ዐርብ የስቅለቱ መታሰቢያ ዕለትሥዕለ ስቅለት ተሠርቶ ለስቅለቱ ነክ የሆኑ ምንባባት ሲነበቡ ይዋላል ። ሠርክ ሲሆን እያንዳንዱ ምእመን ወደ ቄሱ እየቀረበ በወይራ ቅጠል ይጠበጠባል። ቄሱም በወይራ ቅጠል እየጠበጠበ ተጨማሪ ስግደት ይሰጠዋል ። ይህም በወይራ ቅጠል መጠብጠብ የጌታ ግርፋት ምሳሌ ነው ። ቀጥሎም አራት መቶ እግዚኦታ ይደርሳል ። ለበዓሉ የተሠሩ መዝሙራትና ምንባባት ከተደረሱ በኋላ ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ተብሎ መስቀል ከማሳለም በቀር ኑዛዜ ተደርጎ እግዚአብሔር ይፍታ ይባላል ። ጸሎተ አስተሥርዮ ይደረጋል(ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 15፤601) በአሥራ ሁለት ሰዓት ሠርሖተ ሕዝብ ይሆናል ። ሐዋርያት የጌታን ትንሣኤ ሳናይ እህል ውሃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሣኤ አክፍለዋል ። በዚህም መሠረት በቤተ ክርስቲያናችን የሚችል ዓርብንና ቅዳሜን እንዲያከፍል ፡ የማይችል ሰው ግን ቅዳሚትን ብቻ እንዲያከፍል ታዟልዕ (ሉቃ· 5፡33፟35፣ ፍትሕ· መን· አንቀጽ 15፡578)።
ቅዳሜ ጧት ምእመናኑና ካህናቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ የጧት ጸሎት ሲፈጸም «ገብረ ሰላመ በመስቀሉ” ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ ሰላምን አደረገ የምሥራች እየተባለ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰበው ሁሉ ቄጠማ ተባርኮ ይሰጣል ፡ የምሥራች ምልክት ነውና ። ምእመናኑም በራሳቸው ያሥሩታል ።
ወደ ቤተ ክርስቲያን ላልመጡትም ካህናት በየሰበካቸው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው መስቀልና ቃጭል ይዘው ቄጠማውን የምሥራች እያሉ ያድላሉ።
የፊተኛው ቀዳም እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ ከሥራው ያረፈበት ዕለት እንደሆነ ይህ ደግሞ የማዳን ሥራውን በመስቀል ላይ ፈጽሞ ስኩብ በመቃብር ሆኖ የዋለበትና ያደረበት ዕለት ነው ። ይህ ዕለት «ስዑር ቀዳም» ይባላል ። ስዑር መባሉም ባመት አንድ ቀን ስለሚጾም ነው ። «ለምለም ቀዳምም» ይባላል ። በዚህ ቀን ቄጠማ ይታደላልና ቄጠማውም የምሥራች ምልክት መሆኑ ከታረክ ጋር የተያያዘ ነው ። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ዓለም በማየ አይኅ በተጥለቀለ ቀጊዜ የኖኅ መርከብ ማረፊያ አጥታ ስትንሳፈፋ የውሃውን ሁኔታ ለመረዳት ኖኅ ርግብን በመርከቡ መስኮት አሾልኮ ላካት ። እሷም የወይራ ቅጠል ባፋ ይዛለት ተመልሳለች ። ኖኅ በዚህ የወይራ ቅጠል የውኀውን መድረቅ ተረድቶ ተደሰተ ። መርከቡንም ለማሳረፍ ተዘጋጀ ። «የወይራው ቅጠል» ለጥፋት ውሃ መድረቅየም ሥራች መንገሪያ እንደሆነ ሁሉ አሁንም በክርስቶስ ሞት «ማየ ሥራዌ ፡ ማየ ድምሳሴ ፡ ኃጢአት ፡ ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ» የምሥራች ፡ እያለች ቤተ ክርስቲያን ለምእመናን ቄጠማ ታድላለች ። (1 ጴጥ· 3፡19–21)።
ለ) ከዐቢይ ጾም ቀጥሎ ሁለተኛው ጾም የረቡዕና የዓርብ ጾም ነው
ረቡዕና ዓርብ ከትንሣኤ ጀምሮ እስከ ጰራቅሊጦስ እሑድ ድረስ ከሚገኙና እንዲሁም ልደትና ጥምቀት ከሚውሉባቸው ረቡዕና ዓርብ በቀር ዓመት እስከ ዓመት ይጾማሉ ። የሚጾሙበትም ምክንያት አላቸው ።
ረቡዕ፡
ረቡዕ የአይሁድ ሸንጎ ጌታን ዓርብ ዕለት ለመስቀል ምክረ ሞቱን የፈጸመበት ዕለት ነው ። (ዮሐ· 11፡46–53) ። መድኃኔዓለም ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል የተወሰነበትን የሞት ውሳኔ ሁልጊዜ በማስታወስ ክርስቲያኖች በዚህ ዕለት እንዲጾሙ ታዟል ።
ዓርብ :-
ዓርብ እንደሚታወቀው ጌታ የተሰቀለበት በሥጋ የሞተበት ብዙ ዘመን ሲጠበቅ የነበረው ተስፋ የተፈጸመበት ቅዱስ ዕለት ነው ። (ዮሐ‧19፡17–30 ፣ ሉቃ 23፡26–49)። ስለሆነም ልደትና ጥምቀት ከሚውሉባቸው እንዲሁም በበዓለ ሃምሳ ውስጥ ከአሉት ረቡዕና ዓርብ በቀር በየሳምንቱ በጾምና በጸሎት እንዲከበሩ በቤተ ክርስቲያናችን ታዟል ፡ (ፍት‧መን‧አን 15 ፣ ዲድስቅ 29)።
ሐ) ሦስተኛው ጾም የነነዌ ጾም ነው
ይህ ጾም የሦስት ቀን ጾም ነው ። ሰኞ ማክሰኞ ፣ ረቡዕ ። ይህ ጾም «በመባጃ ሐመር» «በኢየዓርግና ኢይወርድ» ስለሚመላለስ ቁጥሩ ከአጽዋማት አዋድያት ነው ። አንድ ጊዜ በጥር አንድ ጊዜም በየካቲት ይሆናል ። የቤተክርስቲያን አባቶች ይህን ጾም የወሰኑት የነነዌ ሰዎች በጾምና በጸሎት ከመዓትና ከጥፋት እንደ ዳኑ (ዮናስ 3፡5–9 ፣ ማቴ 12፡39)። ምእመናንም በጾምና በጸሎት ከፈጣሪያቸው ምሕረትንና በረከትን እንዲያገኙ በማለት ነው
መ) አራተኛው ጾመ ገሃድ ነው
ይህ ጾም በልደትና በጥምቀት ዋዜማ የሚጾም ነው ። ልደትናጥ ምቀት ረቡዕና ዓርብ ሲውሉ በሌሊት ስለሚቀደስና ስለሚበላ በለውጡ በዋዜማው ሐሙስና ማክሰኞ ይጾማል ፣ (ፍት·መን·አን· 15)። ይህም ጾም በያመቱ እንዲጾም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተወስናል ።
ሠ) አምስተኛው ጾም ጸመ ነቢያት ይባላል
የጾሙ ጊዜ ከሕዳር 15 እስከ ታኅሣሥ 28 ቀን ያለው ነው ። ይህን ጾም የምንጾመው ነቢያት በየዘመናቸው ስለ ክርስቶስ መምጣት በናፍቆት ይጾሙና ፣ ይጸልዩ ስለነበር የእነርሱን አርአያ ተከትለን የክርስቶስን ልደት ከማክበራችን ቀደም ብለን ይህን ጾም እንድንጾም በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ተሠርቷል ። (ፍት መን‧አን‧15)።
ረ) ስድስተኛው ጾም ጾመ ሐዋርያት ነው
የሰኔ ጾምም ይባላል ። ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለስብከተ ወንጌል ከመሔዳቸው በፊት የጾሙት ነው ። ምእመናንም እነርሱን ምሳሌ አድርገው ከጰራቅሊጦስ እሑድ ማግስት ጀምረው እንዲጾሙ ቤተክርስቲያናችን ታዛለች ። ይህ ጾም «በኢየዐርግና ኢይወርድ» ስለሚመላለስ የተወሰነ ቀን የለውም ፡ አንዳንድ ጊዜ ከአርባ ቀን ይበልጣል ፡ አንዳንድ ጊዜም ከሠላሳ ቀን ያንሳል ።
ሰ) ሰባተኛው ጾም ጾመ ፍልሰታ ለማርያም ነው
የፍልሰታ ጾም ከነሐሴ 1 እስከ 15 ቀን ያለው ነው ። እመቤታችን ያረፈችው በጥር 21 ቀን 50 ዓ·ም ነው ። ሐዋርያት ሊቀብሩ ወደጌቴ ሴማኒ ይዘዋት ሲሔዱ አይሁድ በታተኗቸው ። በዚህ ጊዜ መላእክት የእመቤታችንን ሥጋዋን ወስደው በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥርጉን አኑረውታል ። (ተአምረ ማርያም ፡ ስንክሳር ነሐሴ 16 ቀን)።
ዮሐንስ በተመስጦ እየሄደ ሥጋዋን ያጥን ነበር ። ለሐዋርያት ይህን ይነግራቸዋል ። ለዮሐንስ ተገልጣ ለእኛ ሳትገለጥ ብለው በነሐሴ ሱባዔ ገቡ ። ሁለተኛው ሱባዔ ሲፈጸም በ14ኛው ቀን መልአክ ሥጋዋን አምጥቶ ሰጥቶአቸው ቀብረዋታል ። በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ተነሥታ አርጋለች (ተአምረ ማርያም፡ ስንክሳር ነሐሴ 16 ቀን)።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንን በረከት ለማግኘት ትጾማለች ። በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይህን ጾም ሕፃናቱ ሳይቀሩ ይጾሙታል ።
በዚህ የአሥራ አምስት ቀን ገዜ ውስጥ የማይጾምና የማይቆርብ ከጣመ ምግብ በመከልከል ጥሬ እየቆረጠው ፣ ውሃ እየጠጡ በጾምና በጸሎት ይሰነብታሉ ። በፍልሰታ ጾም ጊዜ በጠቅላላ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለው ሁኔታ ሕዝቡ ልጅ አዋቂ ሳይል የሚያሳየው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ኢትዮጵያ ለእመቤታችን የቃል ኪዳን አገር መሆኗን ይመሰክራል ።
እነዚህን አጽዋማት ከሰባት ዓመት በላይ ያለ ሁሉ እንዲጾማቸው ተወስኗል ። ቅዳሴ የሚቀደሰውም ከእሑድና ከቅዳሜ በቀር በጾም ወራት ውሎ ነው ።
ጸሎት ሰው በሃይማኖት ፈጣሪውን ያመሰገነና ሥርየተ ኃጢአትን እየለመነ ከፈጣሪው ጋር የሚነጋገርበት ቃል ነው ። (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 14፡528) ። የጸሎት መሠረቱ ፡ «እሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኋል ፣ ደጅ ምቱ ይከፈትላችኋል» የሚለው አምላካዊ ቃል ነው ፡ (ማቴ፡7፡7) ለጸሎት አፈጻጸምም የተለየ ጊዜና ቦታ አለው ። በዚህም መሠረት:- ካህናትና ምእመናን ለጸሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሔዱባቸው ጊዜያት ጥዋትና ማታ ናቸው
የጸሎት ጊዜያት
የጸሎት ጊዜያት ሰባት ናቸው (መዝ. 118፡164)
ሀ)ነግህ
ለ) ሠለስት
ሐ) ቀትር
መ) ተስዓት (ዘጠኝ ሰዓት)
ሠ) ሠርክ
ረ) ሰዓተ ንዋም (የምኝታ ሰዓት)
ሰ) መንፈቀ ሌሊት (ዕኩለ ሌሊት) ናቸው ።
ከ7ቱ ጊዜያት ካህናትና ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔደው የሚጸልዩባቸው ነግህና ሠርክ ናቸው ። በቀሩት ጊዜያት ግን በያሉበት ሊጸልዩ ይገባል (ፍት·መን·አን· 14 ረስጣ 48 ፡ 47 ድስቅ 12) ።
ጸሎት በ3 ይከፈላል ።
- የግል ጸሎት
- የቤተሰብ ጸሎት
- የማኅበር ጸሎት
ሀ) የግል ጸሎት
የግል ጸሎት የሚጸለየው በቤትና በአመች ቦታ ነው ። የግል ጸሎት ማንም ሳያየውና ሳይሰማው አንድ ሰው በግሉ የጸሎት ቤቱን ዘግቶ በስቂለ ኅሊና ሆኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየው እንዲሰማው አድርጎ በኅቡዕ የሚጸልየው ጸሎት ነው፡ (ማቴ 6:5–13) ።
ለ) የቤተሰብ ጸሎት
የቤተሰብ ጸሎት ቃሉ እንደሚያመለክተው አንድ ቤተሰብእ በአንድነት ሁኖ የሚያደርገው ጸሎት ነው ። ለዚህም የመቶ አለቃው የቆርነሌዎስ ጸሎት ምሳሌ ይሆናል ። (የሐዋ·ሥራ· 10፡2–6)።
ሐ) የማኅበር (የቤተክርስቲያን) ጸሎት
የማኅበር ጸሎት የሚባለው ካህናትና ምእመናን ወንዶችና ሴቶች ሽማግሌዎችና ወጣቶች በአንድነት ሆነው በቤተ ክርስቲያንና አመቺ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ ተሰብስበው የሚጸልዩት ጸሎት ነው ።
በብሉይ ኪዳን የነበሩ አማንያን ወደ ቤተ እግዚአብሔር እየሔዱ ይጸልዩ ነበር ። (1ኛ ሳሙ· 1·9 13፡ መዝ· 121·1 ፡ ሉቃ 18፡10–14)።
በሐዲስ ኪዳንም ሐዋርያትና የሐዋርያት ተከታዮች የሆኑት ከርስትያኖች የቤተ ክርስቲያን መነሻዎች በሆኑት በጽርሐ ጽዮን በማርቆስ እናት በማርያም ቤት እንዲሁም በመጀመሪያዋ በአንጾኪያ ቤተክርስቲያን እየተሰበሰቡ ይጸልዩ ነበር (የሐ·ሥ· 1 ፡ 14 ፡ 25 ። 3 ፡ 1 ፡ 12፡12፡13፡1–3) ።
በዚሁ መሠረት በሰንበትና በበዓላት ቀናት ሁሉ ካህናትና ምእመናን በቤተ ክርስቲያን እየተገኙ በሰዓታት በማሕሌትና በጸሎተ ቅዳሴ እንዲያመሰግኑ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አላት ። ሰዓታት በገዳማትና በአድባራት ከዓመት እስከ ዓመት ፡ በገጠርአብያተ ክርስቲያናት በእሑድ ፡ በበዓላትና በጸሎተ ፍትሐት ጊዜ ሌሊት በቤተ ክርስቲያን የሚጸለይ የካህናት የኅብረት ጸሎት ነው ። የመዓልት ሰዓታትም አለ በአጽዋማት ጊዜ በቀን በየሰዓቱ የሚጸለይ (አባ ጊዮርጊስ ሰዓታት ።)
ማሕሌት በዝማሜ በመቋሚያ (ዘንግ) በጸናጽልና በከበሮ የሚዘመርየ ካህናት የኅብረት መዝሙር ነው ። የዐቢይ ጾም ማሕሌት ያለ ጽናጽልና ከበሮ በመቋሚያ ብቻ እየተዘመመ ይዘመራል ። በካህናት መሪነት በምእመናን ተሳታፊነት (ተሠጥዎ ተቀባይነት) የሚፈጸሙ ፡
ጸሎተ ቡራኬ ቤተ ክርስቲያን
ጸሎተ ጥምቀተ ክርስትና
ጸሎተ ሢመተ ክህነት
ጸሎተ ተክሊል
ጸሎተ ምህላ
ጸሎተ ፍትሐት
ጸሎተ ቅዳሴና የመሳሰሉት ናቸው ።
ጸሎተ ቅዳሴ
ጸሎተ ቅዳሴ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት ።
እነርሱም፡
1ኛ– «ኦ እኁየ ሀሉ በዝንቱ ልቡና» ከሚለው አንስቶ ሚመጠ ንግርምት” እስከሚለው የዝግጅት ክፍል ፡
2ኛ– «ሚመጠን ግርምት» ከሚለው አንስቶ ፃኡ ንዑሰ ክስቲያን» እስከሚለው የትምህርት ክፍል ፡
3ኛ– «ፃኡ» ከተባለ በኋላ ያለው ፍሬ ቅዳሴ ነው ፡ የዚህም አፈጻጸምሥርዓት በሥርዓተ ቅዳሴውና በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 12 በዝርዝር የተመለከተው ነው ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥጋውንና ደሙን የምታከብርባቸው አሥራ አራት ቅዳሴያት አሏት ።እነርሱም፡
- ቅዳሴ ሐዋርያት
- » ” እግዚእ»
- » ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ
- » ማርያም
- » ሠለስቱ ምእት
- » አትናቴዎስ
- » ባስልዮስ
- » ጎርጎርዮስ እኍሁ ለባስልዮስ
- » ኤጲፋንዮስ
- » ዮሐንስ አፈ ወርቅ–
- » ቄርሎስ
- » ያዕቆብ ዘሥሩግ
- » ዲዮስቆሮስ
- » ካልእ ጎርጎርዮስ ናቸው ።
የግልም ሆነ የማኅበር ጸሎት አፈጻጸም
በጸሎት ጊዜ ፡
ሀ) ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎመቆም ነው ። (መዝ፡5፡3)።
ለ) ወገብን መታጠቅ፣ ልብስን ዝቅ አድርጎ ማደግደግ ነው (ሉቃ· 12፡35 ፣ ፍት·ን· አንቀጽ 14 ።
ሐ) በጸሎት ጊዜ ፊትን ወደ ምሥራቅ መልሶ መቆም ወዲያና ወዲህ ወደ ግራ ወደ ቀኝ ፡ ወደ ሌላም አለማለት ፡ በሰፊሐ እድ ፡ በሰቂለ ሕሊና ፡ ሁኖ መጸለይ ይገባል (መዝ· 133፡2፡ ዮሐ· 11፡41)።
መ) ጸሎት ሲጀመርና ሲፈጸም አመልካች ጣትን ከሌሎች ጣቶች ጋር አመሳቅሎ በትእምርተ መስቀል አምሳል በጣት ማማተብ ነው ፡ ሲያማትቡም ከላይ ወደ ታች ከግራ ወደ ቀኝ በማድረግ ነው ። በማማተብ ጊዜ የክርስቶስን መከራ መስቀል ማሰብ ያስፈልጋል ። (ሉቃ 11፡20) ።
ሠ) የሚጸልይ ሰው በትሕትናና በጸጥታ ሁኖ ለሌላ ሰው እንዳይሰማ ለራሱ ጆሮ ብቻ እንዲሰማ አድርጎ ኃጢአቱን እያሰበ መጸለይ ይገባዋል ይህንም የሚያደርገው ስለአለፈው ኃጢአቱና በደሉ ነው ፡ ( ሳሙ· 1:3)
ረ) የሚጸልይ ሰው በጥቡዕ ልብ በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገራል ፡ አሳቡን በእግዚአብሔር ላይ ይጥላል ፡ የዓለምን አሳብ ሁሉ ይተዋል ።
ሰ) የሚጸልይ ሰው ሲያማትብ “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አዐትብ ገጽየ ወኩለንታየ በትእምርተ መሰቀል” እያለ ነው ። ሁለተኛም «እግዚኦ መሐረነ እግዚኦ መሐከነ እግዚኦ ተሣሃለነ ወባርከነ አሜን» እያለ ያማትባል ። ሦስተኛም «ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም አሜን ፡ እግዚኦ ረስየነ ድልዋነ ከመንበል በአኰቴት አቡነ ዘበሰማያት» የሚለውን ጸሎት 3 ጊዜ እየደገመና እየሰገደ በማማተብ በጸሎት መጀመሪያና መጨረሻ ጊዜ ማድረግ አለበት ። እንዲሁም መስቀልን ከሚያነሣ ቃል ሲደርስ ማማተብ ፣ ስግደትንም ከሚያነሣ ቃል ላይ ሲደረስ መስገድ ይገባዋል ።
ሸ) የጸሎቱ ቅደም ተከተል መጀመሪያ አቡነ ዘበሰማያት ፡ ሁለተኛ መዝሙረ ዳዊት ፡ ውዳሴ ማርያምና ሌሎችም ፡ ቀጥሎ አቡነ ዘበሰማያት ጸሎተ እግዚእትነ ማርያም ፣ ጸሎተ ሃይማኖት በመጨረሻም አቡነ ዘበሰማያት ፡ ኪርያላይሶን 41 ጊዜ ይባላል ። ክርስቲያን ሁሉ መጸለይ አለበት ። የማያውቅ ምእመን ተምሮ መጸለይ ግዴታው ነው ካህናት ግን ሁሉንም እንዲጸልዩ ታዝዘዋል ። (ኤፌ. 5፡19–20 ፡ ማቴ· 7:7–8) ።
ቀ) ሲጸልይ ማዘን ማልቀስ ይገባዋል ፡ ሲያለቅስም በደሉንና ኃጢአቱን እያሰበ ለየአንዳንዱ በደል ዕንባን ማፍሰስ ነው ።
በ) የሚጸልይ ሰው በጸሎት ላይ ሳለ ጸሎቱን አቋርጦ ከማንም ሰው ጋር ፈጽሞ መነጋገር የለበትም ፡ ጸሎቱን ለማቋረጥ ችግር ቢገጥመው ግን በአቡነ ዘበሰማያት አሥሮ ንግግሩን ሲፈጽም ከአቋረጠበት ተነሥቶ ጸሎቱን ሊጸልይ ይገባል ።
ጸሎተ ምህላ
ይህ ጸሎት በአገር ላይ አባር ቸነፈር ፡ ጦርነት ሲነሣና ለማኅበረሰብእ አስጊ የሆነ መቅሠፍት በተከሠተ ጊዜ እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት ፣ ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ የምሕረትና የይቅርታ መለመኛ ነው ። (ዘኁ· 1 ፡ 46–50 ፡ ትንቢተ ዮናስ 3፡5110 ፣ ኢዩ ·2፡12–19 ፣ 1ነገ· 8:22–53)።
በመሆኑም የተለየችግር ባጋጠመ ጊዜ ምእመናን ሁሉ በየሰበካ ቤተክርስቲያናቸው በጥዋትና በማታ እየተገኙ በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን እንዲለምኑ ቤተ ክርስቲያን ታዛለች ።
ጸሎተ ፍትሐት
ቤተ ክርስቲያን ለሙታን ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ ታዝዛለች ። ፍትሐት ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ የሚለዩት ሰዎች ከማዕሠረ ኃጢአት እንዲፈቱ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ጸሎት ነው ።
ጸሎተ ፍትሐት ሥርየተ ኃጢአትን ፡ ይቅርታን ፡ ዕረፍተ ነፍስን ያሰጣል ። ለደጋጎቹም በክብር ላይ ክብርን ተድላ ዕረፍትን ይጨምራል። ሙታንና ሕያዋን የሚገናኙት በጸሎት አማካይነት ነው። «ሕያዋን ለሙታን ይጸልያሉ ፣ ሙታንም ለሕያዋን ይለምናሉ ። » (ሄኖክ 12፡34) በነፍስ ሕያዋን ናቸውና ፡ (ማቴ 22፡31–32 ፣ ሉቃ· 20፡ 37–39 ። ባሮክ 3:4)
ለሙታን ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግላቸው ፡ መሥዋዕት እንዲሠዋላቸው ፡ በቤተ ክርስቲያንና በመካነ መቃብራቸው እንዲጸለይላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት አዝዘዋል ። «በክርስቶስ አምነው ስለሞቱ ወንድሞቻችሁ ክርስቲያኖችና ሰማዕታት በቤተ ክርስቲያን ያለ ሀኬት ተሰብሰቡ ፡ በቤተ ክርስቲያን መሥዋዕት ሠዉላቸው ፡ ወደ ቤተ ክርስቲያንና ወደ መቃብር ስትወስዱአቸውም መዝሙረ ዳዊት ድገሙላቸው (ዲድስቅልያ አንቀጽ 33) ።
የቤተ ክርስቲያን የሕግና የሥርዓት መጽሐፍ ፍትሕ መንፈሳዊም በዲድስቅልያ የተጠቀሰውን ያጸናል ። (አንቀጽ 22) ። በዚሁ መሠረት ቤተ ክርስቲያናችን ለሞቱ ሰዎች ከዐእተ ነፍስ እስከ ርደተ መቃብር ከቤት እስከ ቤተ ክርስቲያን አስፈላጊውን ጸሎትት ጸልያለች ፡ መዝሙረ ስብሐት ታደርሳለች ።
ለሙታን የሚደረገው መታሰቢያም ከዕለተ ሞት እስከ አመት ከዚያም በላይ ሲሆን ፡
- በዕለተ ሞት
- በሣልስት
- በሰባት
- በአሥራ ሁለት
- በሠላሳኛው ቀን
- በዓርባኛው ቀን
- በሰማንያኛው ቀን
- በስድስተኛው ወር (መንፈቅ) በሙት ዓመት በየዓመቱ ጸሎት እንዲጸለይላቸው ፡ ዕጣን እንዲታጠንላቸው መሥዋዕት እንዲሠዋላቸውና መታሰቢያ እንዲደረግላቸዉ ምጽዋት እንዲመጸወትላቸው ቤተ ክርስቲያናችን ታዛለች (ፍት· መን· አን· 22) ።
ከዚህም ሁሉ ጋር፡
- ስለ ሕሙማን
- ስለ መንገደኞች
- ስለ ዝናመ ምሕረት
- ስለ ምድር ፍሬ
- ስለ ወንዞች ውሃ
- ስለ ሙታንና ስለሕያዋን
- ስለ ንዑሰ ክርስቲያን
- ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት
- ስለ ሀገርና ስለ ዓለም ሰላም
- ስለ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች
- ስለ ሀገር መሪዎች
- ስለ ነዳያንና ምስኪናን
- ስለ ስደተኞች
- ስለ አዘኑትና ስለተከዙት
- ስለ ታሠሩት
- ስለ በደለኞች (ኃጢአተኞች)
- ስለ ሃይማኖት ጽንዓት
- ስለ ወንዶችና ስለሴቶች ምእመናን በጠቅላላ ስለዓለም ሁሉ ቤተክርስቲያን ትጸልያለች ። ስለዚህም በየዓይነቱ ራሱን ችሎ የሚጸለይ መጽሐፈ ጸሎት አላት፡(መጽሐፈ ቅዳሴ ።)
ምጽዋት ከምግባራት ሠናያት አንዱና ዋነኛው ክፍል ነው ። የምጽዋት መሠረቱ እንጀራህን ለተራበ ስጥ ፤ ድሆችን በቤትህ እሳድር ፣የ ቤትህን ርኁብ ቸል አትበል ፡ የሚራሩ ብፁዓን ናቸው ፡ (ኢሳ 58፡6-8 ። ማቴ· 5፡7) የሚለው ነው ።
ምጽዋት በሁለት ዓይነት መንገድ ይሰጣል ።
ሀ) ቀኝህ የምታደርገውን ግራህ አትወቅ (ማቴ· 6፡1–4) ። በማለት ጌታ በአንቀጸ ብፁዓን በተናገረው መሠረት ሌላ ሁለተኛ ሰው ሳያይና ሳያውቅ የሚሰጥ ነው ።
ለ) በፍትሕ መንፈሳዊ በአንቀጽ 16 እንደታዘዘ በቤተ ክርስቲያን ማዕከልነት የሚሰጥ ነው ።
ምጽዋት ወደ ፍጹምነት የምታደርስ ናት ። (ማቴ· 19፡21–22) ። ምጽዋት ከትሩፋት ሁሉ በላይ ናት (ሆሴዕ፡ 6፡6 ማቴ 12፡7) ። ምጽዋት ሐዋርያዊ ትውፊትነት አለው (1ኛ ቆሮ 16፡1–4 ፣ 2ኛ ቆሮ.9፡6–7 ፣ ገላ 6፡9–10 ፣ ዕብ 13፡16) ።
ከቤተ ክርስቲያን አባቶችም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰው ባለመለየት ለተቸገረው ሁሉ ምጽዋት መስጠት እንደሚገባ አስተምሮአል (ዮሐ·ኣ·ተግ· 10) ። ምጽዋት ርዳታን ለሚሹ ሁሉ የሚሰጥ የገንዘብ ፡ የልብስና የቀለብ ርዳታ ሁሉ ነው። ከተረጂ ወገን ትርፍን ሳይሹ ወይም ይመለስልኛል ብሎ ተስፋ ሳያደርጉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 6፡ 14 በተናገረው መሠረት የሚፈጸም ነው ።
በቤተ ክርስቲያናችን የምጽዋት አፈጻጸም የራሱ የሆነ ይዘት አለው። ይኸውም ምእመናን በሚጾሙበት ወራት ችግረኞችን እንዲጐበኙ (ኢሳ. 58፡6–9።) እንዲሁም በየቤተ ክርስቲያኑ ሰበካ ጉባኤ የችግረኞች መረጃ ክፍል እየተቋቋመ ችግረኞች እንዲረዱ የሚያዝሥርዓት አላት ፡ (ቃለ ዓዋዲ) ። ምጽዋት ኃጢአትን ያስተሠርያል (ዳን· 4፡27 ፣ ሉቃ· 7፡ 47 ፣ ማር· 4፡24) ። ምጽዋት ብፅዕናን ያሰጣል (ማቴ· 5፡7 ፤ የሐዋ· ሥራ 20፡35) ። በዚህና በመሳሰሉት ሁሉ ምጽዋትና ርኅራኄ ማድረግ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ የተለመደና እንደ ሥርዓቱ ሲፈጸም የኖረ አሁንም በመፈጸም ላይ ያለ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው ።
ስግደት ሰው አምልኮቱንና ተገዥነቱን ለመግለጥ ራሱን ዝቅ አድርጎ ግንባሩን መሬት በማስነካት ለፈጣሪው ተገዢነቱን የሚገልጽበት ተግባር ነው። የዚህም መሠረቱ “ለጌታ ለአምላክህ ስገድ” “በቅድስናውስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ” (ዘዳግ· 6፡13 ፣ ማቴ 4፡10 ፣ መዝ 28፡2) የሚለው ነው ። እንዲህ ያለውም ስግደት የአምልኮት ስግደት ይባላል ። የሚቀርበውም ለአምላክ ብቻ ነው (ማቴ 4፡10) ። ለአምላክ የሚቀርብ ስግደትም በእውነት ፡ በመንፈስ መሆን ይገባዋል (ዮሐ· 4፡24) ።
ስግደት በሦስት ይከፈላል ። እርሱም ፡
ሀ) ሰጊድ ፡ ከመሬት ወድቆ ግንባርን ምድር አስነክቶ መነሣት ነው ።
ለ) አስተብርኮ ፡ ጉልበትን ምድር አስነክቶ መነሣት ነው ።
ሐ) አድንኖ ፡ ራስን ወደታች ዝቅ አድርጎ እጅ መንሣት ነው ።
በቤተ ክርስቲያን ስግደት የሚፈጸምባቸው ጊዜያት
ሀ) ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ (መዝ፡28፡2) ።
ለ) ጸሎት ሲጀመር ፥
ሐ) በጸሎቱ መካከል ስግደት ከሚያነሣ ቃል ላይ ሲደረስ ፥
መ) እንዲሁም በጸሎቱ መጨረሻ ላይ መስገድ እንደሚገባ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 14፡35–37 ። በአለው የታዘዘ የአምልኮትመግለጫ ሥርዓት ነው ።
በሰንበት ፡ በበዐለ ሐምሳ ፡ በጌታችንና በእመቤታችን እና በሌሎችም ዐበይት በዐላት ፡ ሥጋውንና ደሙን ከተቀበሉ በኋላ ፡ ከአድንኖና ከአስተብርኮ በቀር ስግደት አይሰገድም ፣ (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 14:537) ስግደት ሁለት ዓይነት ነው ።
እርሱም ፡
1· ለእግዚአብሔር አምላክ የምናቀርበው ስግደት ፡ አስተብርኮና አድንኖ የባሕርይ ስግደት ነው ።በታቦተ ሕጉ ፊትም ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ስግደት የአምልኮት ስግደት ነው ። (ኢያሱ 7፡6 ፤ ፊል· 2፡10) ።
2: ሀ) ለእመቤታችን
ለ) ለቅዱሳን መላእክት
ሐ) ለጻድቃንና ለሰማዕታት
መ) ለመስቀልና ለሥዕል የምናቀርበው ስግደት ፡ አስተብርኮና አድንኖ የጸጋ የአክብሮት ስግደት ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ በዐላት አከባበር የራስዋ የሆነ ሥርዓት አላት ። ከሁሉ በፊት ቤተ ክርስቲያናችን ቅዳሜንና እሑድን ታከብራለች ። የቅዳሜ መከበር በብሉይ ኪዳን ታዞአል (ዘፀ· 20፡8)
በዘመነ ሐዲስ የክርስቲያኖች የቀዳሚት ሰንበት አከባበር እንደ አይሁድ ለሰው የሚከብድ እንዳይሆን ቤተ ክርስቲያን “ኢይደልዎሙ ለክርስቲያን ከመ ያጽርኡ ተገብሮ በዕለተ ሰንበት ከመ አይሁድ አላይትግበሩ ከመ ክርስቲያን ፡ ወኢትትዓቀቡ ሰንበተ ከመ አይሁድ” (ፍት·መን·አን·19።) በሚለው መሠረት እንዲፈፀም ታስተምራለች ። ሰንበተ ክርስቲያን እሑድም ጌታ ከሙታን ተለይቶ ስለተነሣባት የጌታ ቀን ተብላ በሐዲስ ኪዳን የከበረች ዕለት ናት፡ (ራእ· 1:10 ፣ 1ቆሮ· 16:1)።
“ሰንበተ ክርስቲያንን አከበራት ፡ ከፍ ከፍም አደረጋት ፡ የብርሃን ቀን አላት ፡ ከዕለታትም ሁሉ አበለጣት” (ቅዱስ ያሬድ ድጓ ዘፋሲካ።)
እንዲሁም “ወዕረፍትሰ አኮ በሰኪብ ከመ ዘሐመ በደዌ እላ በትጋህ መዓልተ ወሌሊተ ከመ ንኩን ፍቁራነሃ ለዛቲ ዕለት” (ቅዳሴ ኣትናቲዎስ 17–4) በሚለው መሠረት ምእመናን በቤተ ክርስቲያን እየተገኙ በመጸለይ ፡ የተቸገሩትን በመርዳት ፡ የታመሙትን በመጠየቅና የተጣሎትን በማስታረቅ እንዲያከብሩ ታስተምራለች ።
በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የጌታ ዐበይት በዐላት ዘጠኝናቸው ። እነዚህም ዐበይት በዓላት ፡
1ኛ· ትስብእት (ፅንሰት)
2ኛ· ልደት
3ኛ· ጥምቀት
4ኛ· ደብረ ታቦር
5ኛ· ሆሣዕና
6ኛ· ስቅለት
7ኛ· ትንሣኤ
8ኛ· ዕርገት
9ኛ· ጰራቅሊጦስ ናቸው ።
1ኛ· ትስብእት (ዕንሰት) :- ይህ በዓል የሚከበረው መጋቢት 29 ቀን ነው ። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለድንግል ማርያም የአምላክን ከርሷ ሰው መሆን ያበሠረበት ዕለት ነው ። በመንጸፈ ደይን ወድቆ ለነበረው የሰው ዘር ታላቅ የምሕረት ቀን ነው ።
2ኛ· ልደት :- ልደት በነቢያት ትንቢት የተነገረለት የሰውን ልጆች የፈጠረ ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ፡ ሰውን ለማዳን ሰው ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደበት ዕለት ነው ። ልደት በየዓመቱ የሚከበረው ታኅሣሥ 29 ቀን ነው። በዘመነ ዮሐንስ ግን (የሉቃስ ጳጉሜን ስድስት ስትሆን) ልደት ታኅሣሥ 28 ቀን ይከበራል ።
3ኛ· ጥምቀት :- ክርስቶስ በተወለደ በ30 ዓመቱ ተጠምቆ ሥራውን ጀምሯል ። ጌታ የተጠመቀው በፈለገ ዮርዳኖስ ነው ፤ ያጠመቀውም ዮሐንስ ወልደ ዘካርያስ ነው ። በተጠመቀም ጊዜ አብ በደመና ሁኖ የምወደው ልጄ ይህ ነው፡ብሎ መስክሮለታል ፡ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀምጧል ። (ማቴ· 3፡1–17 ፣ ማር· 1፡4–12 ፣ ሉቃ· 3፡22 ፣ ዮሐ· 1፡29-34) ።
ይህ በዓልም በሚከበርበት ጊዜ በዋዜማው ታቦታቱ ከየቤተክርስቲያናቸው ወጥተው በወንዝ ዳር በዳስ ወይም በድንኳን ያድራሉ። ሌሊት ስብሐተ እግዚአብሐር ሲደርስ አድሮ ሥርዐተ ቅዳሴው ይፈጸማል። ሲነጋ በወንዙ ዳር (በግድቡ) ጸሎተ አኰቴት ተደርሶ አራቱም ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ውሃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል ። ይህም ጥምቀትን ለመድገም ሳይሆን የጌታችንን ጥምቀት ለማስታወስና በረከትን ለመቀበል ነው ። ጥምቀት የሚከበረው በያመቱ ጥር 11 ቀን ነው ።
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በያመቱ ይህን የምትፈጽመው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፡ በነቢያት የተነገረውን ትንቢት ለመፈጸም ፡
= ውሃን ለመቀደስ
= ለጥምቀት ኃይልን ለመስጠት
= ለእኛ አርአያና ምሳሌ ለመሆን ያሳየውን ትሕትና ለመመስከርናለማስተማር ነው ።
4ኛ· ደብረ ታቦር :- ደብረ ታቦር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማስተማር በነበረበት ጊዜ በደብረ ታቦር ላይ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ዕለት ነው (ማቴ·17፡1–9)። ይህ በዐል በያመቱ ነሐሴ 13 ቀን ይከበራል ።
5ኛ· ሆሣዕና :- ሆሣዕና ከትንሣኤ አንድ ሳምንት ቀድሞ በሚውለው እሑድ የሚከበር ዐቢይ በዐል ነው ። ታሪኩ በወንጌል ተጽፎአል (ማቴ· 21፡9–15) ።
ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው ። በዚያች ዕለት ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ “ሆሣዕና በአርያም” እያሉ ስላመሰገኑት ዕለቱ በጌታ ስም ተጠርቷል ። በዚህ በዐል ጸበርት “ዘንባባ” እየተባረከ ለሕዝ ብይታደላል። ሕዝቡም ጸበርቱን እየተቀበለ እንደ መስቀል አድርጎ እየሠራ በየቤቱ ይሰቅለዋል ፡ በራሱም ያስረዋል ። በዚህ በዐል በቅዱስ ያሬድ የተዘመሩት መዝሙራት እየተዘመሩ በቤተ ክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ።
6ኛ· ስቅለት :- የስቅለት በዓል ለዓለም ቤዛ ሊሆን መድኃኔዓለም ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕለት ነው ።
7ኛ· ትንሣኤ :- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ ፡ ተቀበረ ፡ በሦስተኛውም ቀን መግነዝ ፍቱልኝ ፡ መቃብር ክፈቱልኝ ፡ ሳይል ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ። ይህም የትንሣሌ ዕለት ለክርስቲያኖች የድልና የነፃነት ቀን ነው።
የትንሣኤ በዐል በቤተ ክርስቲያናችን በጣም በደመቀ አኳኋን በመንፈሳዊ ተመስጦ ይከበራል ። ቅዳሜ ማታ ለእሑድ አጥቢያ ሕፃኑ ፡ ሽማግሌው ፡ ወጣቱ ፡ ባልቴቱ በየሰበካ ቤተ ክርስቲያናቸው ይሰበሰባሉ። ሥርዐተ ጸሎት ይጀመራል ።
ለትንሣኤ በዐል በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተሠራው ሥርዓተ ጸሎት ከተከናወነና ኪዳን ከተደረሰ በኋላ ካህኑ መስቀሉን ይዞ ፡
ክርስቶስተንሥአ እሙታን ፡
በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን ፡
አሰሮ ለሰይጣን ፡
አግዐዞ ለአዳም፡
ሰላም ፡
እምይእዜሰ
ኮነ
ፍስሓ ወሰላም የሚለው የትንሣኤው የምሥራችና የምስክርነት ቃል በማስተዛዘል ከተባለ በኋላ የመስቀል መሳለሙ ሥርዓት ይቀጥላል ።
በመንፈቀ ሌሊት ጸሎተ ቅዳሴ ይጀመራል ። ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ሠርሖተ ሕዝብ ይሆናል ።ከእሑድ ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉት ዕለታት እንደ አንድ የትንሣኤ ዕለት ናቸው ።
8ኛ· ዕርገት :- ዕርገት ጌታ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ እስከ ዓርባ ቀን ድረስ ለሐዋርያት እየተገለጠ ታይቷቸዋል አስተምሯቸዋል ። በተነሣ ባርባኛው ቀን ቀደም አድርጎ እንደነገራቸው ለሐዋርያት አሁንም የመንፈስ ቅዱስን መምጣት ነግሮ ወደ ሰማይ ያረገበት ቀን ነው። ይህ በዐል በቤተ ክርስቲያን በጸሎት በማሕሌት ይከበራል።
9ኛ· ጰራቅሊጦስ :- ጰራቅሊጦስ ጌታ ባረገ ባሥረኛው በተነሣ ባምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደበት ዕለት ነው ።ጰራቅሊጦስ ማለት አጽናኝ ማለት ነው ። ይህ በዐል በብሉይ ኪዳን የእሸት በዐል ነበር (በዐለ ሰዊት።) እሥራኤል የነፃነት በዐላቸውን ከሚያከብሩበት ከበዐለ ፋሲካ (በዓለ ፍሥሕ) ጀምረው አምሳውን ቀን በዐል አድርገው ይሰነብታሉ ። በአምሳኛይቱ ቀን በዐለ ስዊትን (የእሸት በዐላቸውን) ያከብራሉ ።
ጌታ ባረገ ባስረኛው ቀን ከጠዋቱ በሦስት ሰዓት መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ወረደ ። (የሐዋ· 2፡1–5) ። ጌታ የነገራቸው የተስፋ ቃል ሁሉ ተፈጸመ ። ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የሞቱና የትንሣኤው ምስክሮች ሆኑ ፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በነሱ ላይ ሲያድር ለቤተክርስቲያን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ ። ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው “ይህች ዕለት የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን” ትባላለች ።
የጰራቅሊጦስ በዐል ከትንሣኤው በኋላ ባምሳኛው ቀን ይከበራል ። የትንሣኤው ቀለም በቤተ ክርስቲያናችን የሚፈጸመው የጰራቅሊጦስዕለት ነው ።
ዘጠኙ ዐበይት በዐላት ከተግባረ ሥጋ በመታቀብ የሚከበሩ ሲሆኑ የትመጣቸውና እንዲሁም የአከባበራቸው ሥነ ሥርዓት ከዚህ በላይ እንዳየነው ነው ። ከነዚህ ውስጥ “ሆሣዕና ፡ ስቅለት ፡ ትንሣኤ ፡ ዕርገትና ጰራቅሊጦስ፡በዐላት ዐዋድያት” ስለሆኑ በቀን አቆጣጠር መባጃ ሐመርን ተከትለው በኢየዐርግና በኢይወርድ ይመላለሳሉ ። ዕለታቸው ግን አይፋለስም ። ሆሣዕና ትንሣኤ ጰራቅሊጦስ እሑድን ፡ ስቅለት ዐርብን ፡ ዕርገት ሐሙስን አይለቅም ። ሌሎቹ “ትስብእት (ጽንስት) ፡ ልደት ደብረታቦር ፡ ጥምቀት” ግን አዋድያት አይደሉም ። ዕለታቸውም የተወሰነ አይደለም ።
ከዘጠኙ ዐበይት በዐላት ሌላ ዘጠኝ ንኡሳን በዐላት አሉ ። እነርሱም፡
1ኛ- ስብከት
2ኛ- ብርሃን
3ኛ- ኖላዊ
4ኛ- በዐለ ጌና
5ኛ- ግዝረት
6ኛ- ልደተ ስምዖን
7ኛ- ቃና ዘገሊላ
8ኛ- ደብረ ዘይት
9ኛ- መስቀል ናቸው ።
ሀ) ስብከት
ለ) ብርሃን
ሐ) ኖላዊ :-
እነዚህ ሦስት በዐላት ከልደት በፊት በሚውሉ ሦስት እሑዶች የሚታሰቡ ናቸው ።ነቢያት ‘ይወርዳል ይወለዳል’ ብለው በትንቢት ይጠባበቁት የነበረው ክርስቶስ “የዓለም ብርሃን ፡ የነፍሳት ጠባቂ ነው” ለማለት በቤተክርስቲያናችን የመዝሙርና የጸሎት ሥርዐት ከልደቱ ቀደም ብሎ ያሉት ሦስት እሑዶች “ስብከት ፡ ብርሃን ኖላዊ” ተብለው ተሰይመዋል ። አከባበራቸውም በስብሐተ እግዚአብሔር ነው ።
መ) በዐለ ጌና :-
ይህ በዐል የሚከበረው ታኅሣሥ 28 ቀን ነው ። በቤተ ክርስቲያናችን በዐላት ሁሉ ከዋዜማቸው ጀምሮ የሚከበሩ መሆኑ ግልጥ ነው ። ስለሆነም ይህ በዐል የጌታ የልደቱ ዋዜማ በመሆኑ በየዓመቱ የሚከበር ከመሆኑም በላይ በየወሩም “አማኑኤል” (እግዚአብሔር ከእኛ ጋር) ለሚለው ስሙ መታሰቢያ ሁኖ ተሰጥቶአል ።
ሠ) ግዝረት :-
ይህ በዐል የሚውለው ጥር ስድስት ቀን ነው ። በሙሴ ሕግ እንደተጻፈ (ዘሌ·12፡3) ሕፃን ሲወለድ በስምንት ቀኑ ይገዘራል ። ይህን የሙሴን ሥርዓት ለመፈጸም ጌታ በተወለደ በስምንተኛው ቀን ወደ ቤተ ግዝረት ገብቶአል ። ሉቃ· 2፡21 የተወለደው ታህሣሥ 29 ቀን ሲሆን ስምንተኛው ቀን የሚውለው ጥር 6 ቀን ነው ፡ ይህ ቀን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሲከበር ይኖራል ።
ረ) ልደተ ስምዖን :-
ይህም በዐል ጌታ በተወለደ በአርባኛው ቀን የሚከበር ነው ። ጌታ ሥርዐተ ኦሪትን ትንቢተ ነቢያትን ሊፈጽም እንጂ ሊሽር ስላልመጣ ለሙሴ ሕግን የሰጠ ሲሆን የሙሴን ሕግ ፈጽሟል ። ከላይ እንዳየነው በስምንተኛው ቀን ወደ ቤተ ግዝረት ገብቷል አሁን ደግሞ በተጻፈው መሠረት ዘሌ·12 የሙሴን ሕግ ለመፈጸም “ዕጉለ ርግብ ፡ ዘውገ ማዕነቅ” ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዱት ። በዚያም የእሥራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ የነበረው ስምዖን የሚባል ሽማግሌ ክርስቶስን ሳያይ እንደማይሞት ከመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ጌታ በእናቱ እቅፍ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ በእግዚአብሔር ፈቃድ ወጥቶ በእዚያ ስለነበረ ፡ ጌታን ከእመቤታችን ተቀብሎ ታቅፎ በሉቃስ ወንጌል በምዕራፍ ሁለት ከቁጥር 25–32 ያለውን ጸለየ ። ወደ ቤተ መቅደስ የገባበትና በስምዖን ዕቅፍ የታየበት ዕለት በቤተ ክርስቲያን ይከበራል ። ስምዖን ጌታን በታቀፈ ጊዜ ከእርጅናው ስለታደሰ በዐሉ የጌታ ሁኖ ሳለ ልደተ ስምዖን እየተባለ ይጠራል ።
ሰ) ቃና ዘገሊላ :-
ቃና በገሊላ አውራጃ የምትገኝ መንደር ናት በዚች መንደር ጌታ በሠርግ በዐል ላይ ተገኝቶ ነበር ። (ዮሐ· 2፡11–12)። ይህ ዕለት የጌታ የመጀመሪያ ተአምር የተገለጠበት ስለሆነ በታላቅ ሥነ ሥርዐት እናከብረዋለን ። ይህ በዐል የሚውለው በየካቲት 23 ቀን ነበር ፥ ጌታ ዕለቱን ተጠምቆ ዕለቱን ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዷል ። ከተመለሰ በኋላ በሦስተኛው ቀን ወደ ሠርግ ቤት ተጠርቶ የካቲት 23 ቀን ውሃውን የወይን ጠጅ በማድረግ የመጀመሪያውን ተአምር አሳይቷል ። (ዮሐ· 2፡1–12)። አሁን ግን በዐልን ከበዐል ጋር ለማገናኘት ሲባል በተሠራው ሥርዓት መሠረት የጥምቀት በዐል በዋለ በነጋው ጥር 12 ቀን እናከብረዋለን ።
ሸ) ደብረ ዘይት :-
ደብረ ዘይት የወይራ ዛፍ የመላበት ተራራ ማለት ነው ። የሚገኘውም በኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ 75 ሜትር ያህል ራቅ ብሎ ነው ። ጌታ ቀን በቤተ መቅደስ ሲያስተምር ደቀ መዛሙርቱ የዳግም ምጽአቱን ምሥጢር አንሥተው ጠይቀውት ምልክቱን ገልጦ ነግሮአቸዋል። (ማቴ· 24)።
የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ ቅ/ያሬድም የዐቢይ ጾምን እኩሌታ እሑድ የጌታ ዳግም ምጽአት መታሰቢያ አድርጎ መዝሙሩን በዳግም ምጽአት ደርሶታል ። ዕለቱም ደብረዘይት ይባላል ። ስለዚህ ይህ በዐል ስለክርስቶስ ዳግም ምጽአት ፡ ስለዓለም ፍጻሜ ስለትንሣኤ ሙታን የሚነገርበት ዕለት ነው ።
ቀ) መስቀል :-
የመስቀል በዐል የሚከበረው መስከረም 17 እና መጋቢት 10 ቀንነው ። ታሪኩም በመጠኑ እነሆ ፥ ጌታ በመስቀል ላይ ሙቶ ከተነሣ በኋላ ሕሙማን መስቀሉን እየዳሰሱ በመስቀሉ እየታሹ ይፈወሱ ነበር ። በዚህም ተአምራት እየተሳቡ ብዙዎች ክርስቲያን ሆኑ ። ይህን ያዩ አይሁድ መስቀሉን ባንድ ጥራጊ ማጠራቀሚያ ቦታ ጣሉት ። በየቀኑ የአካባቢው ኗሪ ሁሉ ጥራጊ ስለሚጥለበት ያ ቦታ እንደኮረብታ ሆነ ። ምንም እንኳ ለማውጣት ባይችሉ ክርስቲያኖቹ ያን ቦታ ያውቁት ነበር ።
ከጊዜ በኋላ በጥጦስ ወረራ 70 ዓም ክርስቲያኖቹ ኢየሩሳሌምን ጨርሰው ለቀው ስለወጡና የከተማዋም መልክ ፈጽሞ ስለተለወጠ መስቀሉ የተዳፈነበት ቦታ ወዴት እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም ። በዚህም ምክንያት ከሦስት መቶ ዓመት በላይ ተዳፍኖ ቆይቷል ። በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (327) የንጕሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ይህን ታሪክ ትሰማ ነበርና አስቆፍራ ለማስወጣት ጉዞዋን ወደ ኢየሩሳሌም ቀጠለች ። እዚያም ደርሳ ኮረብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን አላገኘችውም ። ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅላት አላገኘችም ። በመጨረሻ ግን የመስቀሉ መውጣት የእግዚአብሔር ፈቃዱ ነበርና አንድ አረጋዊ ስሙ ኪርያኮስ የሚባል (ኪራኮስ ያሬድ ድጓ ዘዕሌኒ) የዕሌኒን መቸገር አይቶ እንደሚከተለው ይመክራታል ። “አንቺም በከንቱ አትድከሚ ሰውም በከንቱ አታድክሚ እንጨት አሰብስበሽ ከምረሽ ዕጣን አፍሺበት በእሳትም አያይዢው ፥ የዕጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው ፥ በዚህ ምልክት ታገኝዋለሽ” አላት ፥ (ስንክሳር መጋቢት 10) እሷም ያላትን ሁሉ አደረገች ። “ዘዕጣን አንጸረ ሰገደ ጢስ” (ድጓ ዘዕሌኒ) የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አሳየ ፥ ያን ምልክት ይዛ አውጥታዋለች ። “በጎልጎታ ዘደፈኑ አይሁድ ዮም ተረክበ ዕፀ መስቀል ” (ድጓ ዘዕሌኒ) ። ይህን በዓል በመላው ዓለም ያሉ ክርስቲያኖች ያከብሩታል ። በሀገራችን በኢትዮጵያ ግን የላቀና ልዩ የሆነ የአከባበር ሥርዐት አለው ። የመስቀል በዐል ከጥቢ ወራት መግቢያ ጋር የተያያዘ ስለሆነ የተለየ ድምቀት አለው ።
መስከረም 16 በከተማም ሆነ በገጠር በየአካባቢው “መስቀል አደባባይ መስቀል ተራራ” ተብሎ በተወሰነውና በተከበረው ቦታ ሕዝቡ ከየቤቱ ችቦውን እንጨቱን እያመጣ ይደምራል ። ካህናቱም በደመራው ፊት ለፊት ጸሎት አድርሰው “መስቀል አብርሀ ፥ በከዋክብት አሠርገወ ሰማየ እምኵሉሰ ፀሐየ አርአየ” እያሉ ደመራወን እየዞሩ ይዘምራሉ ። ቀጥሎም ሕዝቡ ፡ “ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ” እያሉ ደመራውን ይዞራሉ ሕዝቡ በየደጁ ችቦውን እያበራ ደስታውን ሲገልጥ ያመሻል ። በአሥራ ሰባት ጧት ደመራው ይለኮሳል። በአዲስ አበባና በአንዳንድ ክ/ሀገር በ16 ማታ ደመራው ይለኮሳል። አመድ እስኪሆን ድረስ ይቃጠላል። ደመራው የተጸለየበትና የተባረከ ስለሆነ ሕዝቡ ሕመቱንና ትርኳሹን እየተሻማ ወደየቤቱ ይዞ ይሔዳል ፤ ሰውም ከብትም ይቀባዋል ።
ንግሥት ዕሌኒ መስከረም 17 ቀን ማስቆፈር ጀምራ መጋቢት 10 ቀን መስቀሉ ስለተገኘና ስለወጣ መስከረም 17 እና መጋቢት 10 ቀን እንደ አንድ በዐል ተቆጥሮ ይከበራል ።
ከነዚህ ሌላ የእመቤታችን ሠላሣ ሦስት በዐላት በዓመት በኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ሲከበሩ የኖሩ ናቸው ። አሁንም ይከበራሉ። እንዲሁም በየወሩ በ29 የሚውለው በዓለ እግዚእ ፥ በ12 የሚውለው የቅዱስ ሚካኤል በዐል ፥ እንዲሁም የሐዋርያት በዐለ ዕረፍት ይከበራሉ ።
የዓመት በዐላት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚከበሩት በሥርዐተ ዑደት ነው ። ለበዐሉ የተዘጋጀው መዝሙር እየተዘመረ ታቦቱ ከመንበሩ ተነሥቶ ቤተ ክርስቲያኑን ሦስት ጊዜ ከዞረ በኋላ ትምህርት ተሰጥቶ ሠርሖተ ሕዝብ ይሆናል ። ይህ የሚሆነው ጧት በሚቀደስባቸው ዕለታት ነው ። ውሎ ቅዳሴ ከሆነ ግን ዑደት ተደርጎ ትምህርት ከተሰጠ በኋላ ታቦቱ ሲመለስ ጸሎተ ቅዳሴ ይጀመራል ። ጸሎተ ቅዳሴው ሲፈጸም ሠርሖተ ሕዝብ ይሆናል ።
የአጽዋማትና የበዐላት ኢየዓርግና ኢይወርድ የሚገኝበት ትምህርት “ባሕረ ሐሳብ” (መርሐ ዕውር) በተሰኘው የቁጥር መጽሐፍ ነው ።
በየዓመቱ በኢየዐርግና በኢይወርድ የሚመላለሱት አጽዋማትና በዐላት የሚውሉበት ዕለት የሚታወጀውም መስከረም 1 ቀን በርእሰዐውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ ዕለት ነው ።
የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ ወይም የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ወር መስከረም ነው ። ይህም የጥፋት ውሃ መጉደል የጀመረበትና ከጥፋት ውሃ በኋላ የክረምትና በጋ መፈራረቅ እንደማያቋርጥ እግዚአብሔር ለኖኅ ቃልኪዳን የሰጠበት ወር ነው ። (ዘፍ· 8፡13–22 ፥ ኩፋሌ 7፡19-30)። የዕብራውያንና የግብፅ ዘመን መለወጫም ይኸው መስከረም ነው ። ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊትና የብሉይ ኪዳን ትውፊት ያላት ስለሆነች ፡ ወሩም የዘመን መለወጫ እንዲሆን የተሰጠው ምክንያት ትክክለኛ በመሆኑ ይህን ሥርዐት ጠብቃና አስጠብቃ ትኖራለች ።
ሥዕል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ የአክብሮት ሥርዐተ ትምህርት አለው ። ሥዕል ከክርስትና በፊት በቤተ አይሁድ የታወቀና ከአምልኮት ጋር የተያያዘ ነበር ።
በብሉይ ኪዳን በታቦተ ሕጉ ላይ ሥዕለ ኪሩብን እንዲሥል ራሱ እግዚአብሐር ሙሴን አዞታል ። (ዘፀ· 25፡19 ፥ 37 ፡7 ፤ 1ኛ ነገ· 6፡23 ፤ 2ኛ ነገ· 6፡2-17 ፤ ሕዝ· 9፡3 ፥ 10፡3 ፤ ሄኖክ 14፡11) ። እነዚህ የኪሩቤል ሥዕሎች ከታቦቱ አይለዩም ፡ ምክንያቱም ታቦት የእግዚአብሔር መገለጫ ዙፋን ስለሆነ ነው ሥዕለ ኪሩቤልም የፀወርተ መንበር ኪሩቤል አምሳል ነውና ። የሚሣሉትም እንደሚናተፍ አውራ ዶሮ ሁነው ነው ።
ሥዕል በቤተ ክርስቲያን የተጀመረበት ታሪካዊ ምክንያት አለው ። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚታወቀው የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ትምህርታቸውን ያስፋፉት ዋሻ ፈልፍለው ጉድጓድ ቆፍረው በዋሻ በፍርኩታ (ካታኮምፕ) ግበበ ምድር ውስጥ ነው ። ከዚህም ግበበ ምድር ውስጥ የሰማዕታትን አፅም እየሰበሰቡ ጸሎት ይጸልዩ ፡ ትምህርት ያስተምሩ ነበር ። በዚህም አማኞች እየመጡ የማኅበሩ አባል መሆን ጀመሩ በዚህ ጊዜ የክርስትናን ትምህርት አስፋፍቶ ለማስረዳት በቂ መጻሕፍት ስላልነበሩ እንደ ልብም ወጥቶ ለመፈለግና ለማዘገጀት ነፃነት ስለአልነበራቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ምሳሌዎችን በሥዕል እያቀረቡ ማስተማር ጀመሩ ።
ሥዕሎችንም የሚሥሉት :-
እረኛው በጉን እንደተሸከመ አድርገው ነው ። ይህም “ክርስቶስ በእርሱ ያመኑትን በእርሱም አምነው የሞቱትን ሁሉ የሚያድናቸው ቸርና ታማኝ ጠባቂ መሆኑን ለማስረዳት” ነበር ። ሌላው ሥዕላቸውን የሚጀምሩት በብሉይ ኪዳን ታሪክ ነበር ። ለምሳሌ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አዳምና ሔዋን እንዴት እንደተሳሳቱና ያሳሳታቸውንም እባብ በመካከላቸው አድርገው ነበር ። (ዘፍ· 3፥1–7) በምህላና በጸሎት ላይ ያለችን የምእመን ነፍስ በመርከብ ውስጥ ያለውን ኖኅን አስመስለው ይሥሉአት ነበር ። (ዘፍ· 7፤1–24) ።
ከዚህም ጋር የሐዲስ ኪዳንን ታሪክ በዚሁ
- ግበበ ምድር የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ማብሰር ፡
- የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በይሁዳ አውራጃ በዳዊት ከተማ ቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ መወለድ ፡ ሰብአ ሰገል በቤተ ልሔም ዋሻ ለተወለደው ሕፃን ክርስቶስ አምኃ ሲያቀርቡ ፡
- የጌታ ጥምቀትና የሦስት ዓመታት ከሦስት ወራት ትምህርት ጋር የሠራውን ተአምራት ፡
- በገሊላ አውራጃ በቃና ስለተደረገው የመጀመሪያው ተአምር ፡
- የጌታ ስቅለቱን ሞቱን ፡ ትንሣኤውን ፡ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን ፡
- እመቤታችን ምስለ ፍቁር ወልዳ በግራዋ በኩል ኢሳይያስ ወደ እስዋ እያመለከተ “ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ” ብሎ የተናገረላት ይህች ናት እንደ ማለት ነው ።
ይህንና ይህን የመሳሰሉ በጥንት የክርስቲያኖች መሸሸጊያ ዋሻዎች ተሥለው ተገኝተዋል ። ይህ ሁሉ የተደረገው ከላይ እንደተገለጸው የሃይማኖትን ታሪክ ለማስተማር ነው ።
በሌላም በኩል ስለጌታ ሥዕል ብዙ ታሪክና ትውፊታዊ ትምህርት አለ ። ከሚነገሩት ታሪኮችም አንዱ የጌታን የነገረ መስቀሉን ታሪክ ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሣለው የሚተረከው ነው ። ዮሐንስ ወንጌላዊ በዕለተ ዓርብ እንዳየው አድርጎ ጌታን ሥሎታል ። ስዕሉም “በከመሰቀሉኒ አይሁድ ቅድመ ዕራቅየ በኢየሩሳሌም ዳግመ ትሰቅለኒኑ በሮም” የሚል ድምጽ አሰምቷል ። ወዲያውም ከለሜዳ አስታጥቆ ሥሎታል ። ከለሜዳ አሳታጥቆ መሣል የመጣም ከዚያ ወዲህ ነው ። ዮሐንስ ወንጌላዊም ሥሎ ሲጨርስ ሥዕሉን ቢስመው ከንፈሩ ከሥዕሉ ጋር ተጣብቆ ቆይቶአል ። ይህ ሁሉ ከሥዕሉ የታየው ተአምራት ነው ።
የእመቤታችንን ሥዕል በመጀመሪያ የሣለ ወንጌላዊው ሉቃስ ነው ። በእኛም ቤተ ክርስቲያን የጸሎትና የመዝሙር መጻሕፍት የእመቤታችንን ሥዕል ወንጌላዊው ሉቃስ መሣሉን ይናገራሉ ።
“ሰላም ለሥዕልኪ እንተ ሠዐላ በእዱ ፡ ሉቃስ ጠቢብ እምወንጌላውያን አሐዱ” ይላል ። (መልከዐ ሥዕል ፡ ስንክሳር ጥቅምት 22 ቀን) ።
ሥዕል በቤተ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት መልእክት አለው ። ከእነዚህም አንዱ ተአምራት ነክ የቅዱሳት መጽሕፍትን ታሪኮች ማንበብ ለማይችሉ ሰዎች ለማስረዳት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማንንም ሳይፈራና ሳያፍር ስለሃይማኖቱ መስክሮ በሰማዕትነት የሞተ ወይም ስለ ዓለምና ስለራሱ በመጸለይ መላ ሕይወቱን ከፍትወታት እኩያት ከአጋንንት ጋር በመጋደል ያሳለፈውን ሰማዕት ወይም ጻድቅ በሥዕል ለማስታወስ በሥዕሉም አማካይነት እያንዳንዱ ምእመን ለሥዕሉ ባለቤት ያለውን ክብርና ፍቅር ለመግለጥ ነው ።
በሥዕል ፊት ቆሞ መጸለይ ከባለ ሥዕሉ ረድኤትን ፡ በረከትን መለመን ፡ መማጠን ነው ። ለሥዕል የጸጋ ስግደትን መስገድ ፡ ሥዕልን መሳለም ፡ በሥዕሉ አማካይነት ለሥዕሉ ባለቤት ክብርንና ፍቅርን ለመግለጥ ነው ። ይኸውም የቤተ ክርስቲያን ህልወና ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ጥንታዊ ትውፊት ነው ።
በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐት ለተሣሉና በጸሎት ለከበሩ የጌታ ፡ የእመቤታችን ፡ የቅዱሳን መላእክት ፡ ጻጽቃንና ሰማዕታት ሥዕሎች የጸጋ ፡ የአክብሮት ስግደት ፡ አስተብርኮና አድንኖ ማቅረብ እንደሚገባ ቤተ ክርስቲያናችን ታምናለች ፡ ታስተምራለች ። ስለስለ
“ ቅድመ ሥዕልኪ እሰግድ ፡ ወለሥዕለ ወልድኪ እገኒ ።
ማርያም ድንግል ማርያም እመ አዶኒ” (መልክዐ ሥዕል) ።
መስቀል በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ክብር አለው ። መስቀል በነቢያት ትንቢትና ምሳሌ መሠረታዊ ይዘት አለው ።
ትንቢት
“ሐረገ ወይን ኮነ መድኃኒት ዘእምሐሢሦን ይትዝም ወበጎልጎታ የተክል” (መሐልይ 5፡2) ።
“ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፍርሁከ ፡ ከመ ያምሥጡ እምገጸ ቅስት ፡ ወይድኀኑ ፍቁራኒከ”
(መዝ 59፡4) ተብሎ ተነግሮለታል ።
ምሳሌ፡
የኖኅ መርከብ የተሠራችበት እንጨት ። (ዘፍ· 7–6) ።
ሙሴ የፈርዖን መሰግላንን ድል ያደረገበት በትር ። (ዘጸአ· 4፡2– 9 ፤ እርዌ ብርት ዘኁል 21፡9)። የመስቀል ምሳሌዎች ናቸው ።
ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት በፊት መስቀል የመቅጫ ፡ የርግማንና የውርደት ምልክት ነበር ። (ዘዳግ· 21፡23 ፤ 2ኛ ቆሮ· 5፡21 ፤ ገላ· 3፡13) ።
ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት በኋላ ግን የክርስቶስ መስቀል የመንፈሳዊ ነፃነታችን ዓዋጅ የተነገረበት ሰላማዊ ዙፋን (መዝ· 2፡6 እና 7፡44) ስለሆነ ለክርስቲያኖች ሁሉ የነፃነት ናየድል ምልክት ነው።“ገብረ ሰላመ በመስቀሉ” ክርስቶስ ሰላምን ነፃነትን በመስቀሉ አደረገ ። (ኤፌ· 2፡15–17) ።
ታላቁ ቆስጠንጢኖስ በብርሃን ቅርፅ ያየው መስቀል የድል ምልክት ሁኖ ይኖራል ። የመስቀል አማናዊና ምሥጢራዊ ኃይል ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ላመኑ ነው እንጂ ላላመኑ ስንፍና ነው ። (1ኛ ቆሮ· 1፡18 ፤ ፊል· 3፡18) ። እንዲያውም መስቀልን ኃይለ እግዚአብሔር ነው ማለቱ ዋዛ ይመስላቸዋል ። የክርስቶስ መስቀል ለሞት ለአጋንንት መቅጫ ሆኖል ። “በመስቀሉ ዐሮ አግረረ ወልድ ዘዓለመ ፈጠረ”። (ቅዱስ ያሬድ መዋሥዕት) ። ምእመናን በክርስቶስ አምነው በመስቀል አጋንንትን መናፍቃንን ፍትወታት እኩያትን ድል ሲያደርጉ ይኖራሉና ።
ከዚህ የተነሣ የክርስቲያኖች ኪነ ጥበብ ሁሉ ምልክቱ መስቀል ሆነ በልብሳቸው በመጽሐፋቸው በቤት ዕቃቸው ሁሉ የመስቀል ምልክት አለበት ።
በሀገራችንም ጥልፉ ዝምዝሙ ጌጣ ጌጡ ሌላው ቀርቶ ክርስቲያኖች በግንባራቸውና በሌላውም አካላቸው በመስቀል ቅርፅ ይነቀሳሉ ። በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ብቻ ሳይሆን ከሞቱ በኋላ መስቀል ከምእመናን አይለይም ። አጽማቸው በሚያርፍበት በመቃብራቸው ላይ ሁሉ የመስቀል ቅርፅ ከዕፅ ወይም ከድንጋይ ይሠራል ። በመቃብራቸውም ላይ መደረጉ መስቀል የሞትና የመከራ ምሳሌ መሆኑ ቀርቶ የትንሣኤና የሕይወት ምልክት መሆኑን ለመግለጥ ነው።
ከዚህ በላይ እንደገለጥነው ሥዕልና መስቀል በክርስቲያኖች ሕይወት ከፍተኛ ክብር ስላላቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በራሷ ኪነ ጥበብ በራሷ ሊቃውንት የተዘጋጁትን ሥዕልና መስቀል በጸሎተ ቡራኬ በማክበር በቤተ ክርስቲያን ምእመናንን ስታገለግልባቸው ትኖራለች ። መስቀል በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ቡራኬ ይባረክበታል ።
ካህናት ሥልጣነ ክህነት ከተቀበለበት ጊዜ ጀምረው መስቀል ይይዛሉ በመስቀል ይባርካሉ ። ምእመናንም ይሳለሙታል ።
በዚህም መሠረት ፡
“መስቀል ኃይልነ ፡
መስቀል ዕንዕነ ፡
መስቀል ቤዛነ ፡
መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ ፡
አይሁድ ክህዱ ንሕነሰ አመነ ወእለ አመነ በኃይለ መስቀሉ ድኅነ”
እያለች ቤተክርስቲያን ትዘምራለች ትጸልያለች ።
ለመስቀልም የጸጋና የአክብሮት ስግደት ፡ አስተብርኮና አድንኖ ማቅረብ እንደሚገባ “ወንሰግድ ውሰተ መካን ኀበ ቆመ እግረ እግዚእነ” (መዝ· 131፡7) ። “ለመስቀልከ ንሰግድ ኦሊቅነ ወለትንሣኤከ ቅድስት ንሴብሕ ኵልነ” (ቅዱስ ያሬድ ጾመ ድጓ) የሚለውን መሠረት በማድረግ ታስተምራለች ።
ንዋያተ ቅድሳት ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ለመፈጸም የሚያስችሉ የከበሩ ንዋያት ናቸው ። ለምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አፈጻጻም አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ንዋያተ ቅድሳት አሉ ።
እነዚህም፡
- ጻሕል ፡ ቅዱስ ሥጋው የሚፈተትበት ነው ።
- ጽዋዕ ፡ ክቡር ደሙ የሚቀዳበት ነው ።
- ዕርፈ መስቀል ፡ ክቡር ደሙ የሚሰጥበት ነው ።
- ማሕፌድ ፡ በጌታ መግነዝ አንጻር ኅብስተ ቁርባኑ የሚሸፈንበት ነው ።
- መሶበ ወርቅ ፡ ኅብስተ ቁርባኑ ከቤተልሔም ወደ ቤተ መቅደስ የሚገባበት ነው ።
- ጽንሐሕ ፣ ለማዕጠንት አገልግሎት የሚውል ነው ።
- ቃጭል ፡ በቅዳሴ መግቢያ ፡ ፃኡ ንዑስ ክርስቲያን ሲባል እግዚኦታ በሚደርስበት ጊዜ ፤ ድርገት በሚወረድበት ጊዜና በሌላም በጸሎተ ምህላ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥበትና ሌሎችም ለምሥጢራተቤተ ክርስቲያን አፈጻጸም አገልግሎት የሚውሉ ሁሉ ናቸው ።
እነዚህ ሁሉ ንዋያተ ቅድሳት ከላይ ለተገለጸው አገልግሎት የሚውሉት በጸሎት ፡ በሜሮንና በቡራኬ ከከበሩ በኋላ ነው ። ንዋያተ ቅድሳትን ለማክበር የሚጸለየው ጸሎትና የቅብዐ ሜሮን አፈጻጸም ሥርዐት በሥርዐተ ቅዳሴ መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል ።
ልብሰ ተክህኖልብሰ ተክህኖ ካህናት ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ለምእመናን ለመፈጸም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጊዜ የሚለብሱት በጸሎት የከበረ በአሠራርም በማስቀመጫም የተለየ የመንፈሳዊ አገልግሎት ልብስ ነው። ይኸውም፡
ሀ) የሚቀደስባቸው አልባሳት በቤተ ክርስቲያን ዕቃ ቤት ሊቀመጡና በንጽሕና ሊጠበቁ ይገባል ። ከዚህ ውጭ በሌላ ቦታ እንዲቀመጡ ለሌላ ጉዳይም እንዲውሉ ያልተፈቀደለትም ሰው እንዲለብሳቸው አልተፈቀደም ። (ሕዝ· 44 ፤ 17 19 ፡ ፍት· መን· አንቀጽ 12) ።
ለ) ካህናት የሚደርቡት ካባ ላንቃ 5 መንዲል (ከልጅ) ያለው እንዲሆን ታዟል ።
ሐ) ካህናት በቅዳሴ ጊዜ የሚለብሱት ልብስ እስከ ተረከዛቸው የሚደርስ መሆን አለበት ። (ፍት· መን· አንቀጽ 12 ፡ በስ)።
መ) ካህኑ ልብሰ ተክህኖ ከመልበሱ በፊት ልኩ የሚሆነውን መርጦ ይለብሳል ፡ ካህን ልብሰ ተክህኖ ከለበሰ በኋላ ማውለቅ አይገባውም ። ቀሚሱ ከረዘመበት ይታጠቀዋል ። (ዘፀ· 28፡243 ፥ ፍት· መን አንቀጽ 12፡በስ)።
ሠ) ካህኑ ልብሰ ተክህኖ ከመልበሱ በፊት ጳጳስ ካለ በጳጳስ አስባርኮ ይለብሳል ። ከሌለ ራሱ ባርኮ ይለብሳል ። ዲያቆናቱም አስባርከው ይለብሳሉ ። እነዚህ ንዋያተ ቅድሳትና አልባሰ ክህነት ሁሉ ወደ ቤተክርስቲያን ከገቡና በጸሎተ ቡራኬ ከከበሩ በኋላ ወደ ሌላ ቦታ ሊወሰዱና ለሌላ ለሥጋዊ አገልግሎት ሊውሉ አይገባም ። (ሕዝ‧ 44፡17– 19 ፥ ፍት‧መን‧አን‧ 12) ።
እነዚህን ንዋያተ ቅድሳት ከቤተ ክርስቲያን አውጥቶ የሚወስድና ለማይገባ ሥራ የሚያውል ቢኖር ፡ እንደ ዖዝያንና እንደ ብልጣሶር ጥፋትንና መቅሠፍትን በራሱ ላይ ያመጣል ። (2ኛ ዜና‧መዋ‧26፡18– 20 ፥ ዳን‧ 5፡ 1–31)።