ሥርዐተ ተክሊል

ሥርዐተ ተክሊል ምን ማለት ነው?

ተክሊል የቤተ ክርስቲያን የጋብቻ ሥርዓት ወይም ቃል ኪዳን ማለት ሲሆን ካህናት በሙሽራውና በሙሽራይቱ ላይ የሚያስፈጽሙት የሕግ ጋብቻ፤ ሊፈርስ የማይችል ነው፡፡ ቃል ኪዳኑን ተክሊል ያሰኘው የሙሽሮቹ ልብስ፣ ጌጡ፣ ሽልማቱ፤ ፈርጡ፣ ቀለበቱ እንዲሁም የአበባው አክሊል ሲሆን በአክሊሉ ስም ተክሊል በመባል ይጠራል፡፡
አክሊል ወይም ተክሊል ማለት ዘውድ ማለት ሲሆን ስያሜውንም የወሰደው ከግብሩ ነው፡፡ ምሥጢሩ ግን በቃል ኪዳኑ ወቅት በሚፈጸሙት የጸሎት ሥርዓቶች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ይኸውም በቅዱስ ጋብቻ ወቅት በልብስ፣ በቀለበት፣ በሙሽራውና በሙሽራይቱ ላይ የሚጸለዩ ልዩ ልዩ የጸሎት ሥርዐቶች አሉ፡፡ በሥርዐተ ተክሊል የሚደረገው ጋብቻ ንጽሕናቸውን ጠብቀው እና በድንግልና ጸንተው ለኖሩ ምእመናን ሲሆን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተክሊል ይደረግላቸው ዘንድ ታዝዟል፡፡ ” እስመ ዝንቱ ብእሲ በረከት ይደሉ ለብእሲ ድንግል ወለብእሲት ድንግልት በጊዜ ተዋስቦ ” ፤ ይህ በረከት (ተክሊል) በጋብቻ ጊዜ ለድንግል ወንድና ለድንግል ሴት ይገባልና (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፳፬ ቁጥር ፱፻፮)፡፡ 
በሥርዐተ ተክሊል ጋብቻቸውን ለሚያከናውኑ ሰዎች ሥርዐተ ተክሊል ሲደርስ፡- ወንጌል ይነበባል፣ ኪዳን ይደርሳል፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በምታዘውና በምትፈቅደው መሠረት ቅብዐ ሜሮን ይደረግላቸዋል እንዲሁም ለሥርዐተ ቀለበቱ የሚያስፈልገው ጸሎት ሁሉ ይከናወናል፡፡ በመጨረሻም በቅዱስ ቁርባን ጋብቻው የሚታተም (የሚከናወን) ሲሆን ይህ ሥርዐት ለሽሮቹ የድንግልናቸው መገለጫ ወይም ክብር ነው፡፡

ለተክሊል ጋብቻ መሟላት ያለባቸዉ ዋና ዋና መስፈርቶች ምንድን ናቸው ?

ዕድሜ

የሚጋቡት ወጣቶች ዕድሜአቸው ትዳር የሚጠብቀውን ሓላፊነት ለመወጣት ብቁ ሊሆኑ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም አስቀድሞ በፍትሐ ነገሥት እንደተገለጠው ሴቷ 15 ወንዱ ደግሞ 18 ዓመት የሞላቸው መሆን አለባቸው፡፡ እንደዚህም ሆኖ ሌሎች ነገሮች ካልተሟሉ ከዚህ በላይ ቢሆን መልካም ነው፡፡

የአእምሮም ሆነ የአካላዊ ብቃት፡-

የሚጋቡት ወጣቶች በአእምሮም ጤነኛ ቢሆኑ አካላቸውም ከጋብቻ በኋላ ለሚፈጸመው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ወይም ከሥነ ልቡናዊ ችግር የተነሣ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም ባይችል የቀረውን ወገን ወደ ሌላ ኃጢአት ይገፋፋልና የግድ አካላዊ ብቃት ሊኖር ያስፈልጋል፡፡ የአእምሮ ሁኔታም በትዳር የሚጠበቅበት ሓላፊነት ወይም ቤተሰብ የማስተዳደር ብቃት ሊኖር ያስፈልጋል፡፡

የኢኮኖሚ አቅም፡

የሁለቱም ተጋቢዎች ወይም ከሁለት አንደኛው ወገን ራሱን የቻለ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ የኢኮኖሚ ዐቅማቸው ቤተሰቡን ለማስተዳደር በቂ መሆኑ ሊረጋገጥም ይገባል፡፡ በርግጥ ይህ ሁልጊዜ ላይሆን ይችላል፤ ፍቅር ካላቸው ሁለቱም ሠርተው ሊያፈሩ ይችላሉና፡፡

ስለ ትዳር ማወቅ

ተጋቢዎች ከመጋባታቸው በፊት ስለ ትዳር በአጠቃላይም ስለተክሊል ጋብቻ በሚገባ ሊያውቁ ያስፈልጋል፡፡ ትዳር በሌላ በሦስተኛ ሰው ግፊት የሚፈጸም ወይም ሌላው ስላደረገው ብቻ እስቲ ልሞክረው ተብሎ የሚገባበት ሕይወት አይደለም፡፡ ስለዚህ ከገቡበት በኋላ እንዳይቸገሩ ወጣቶች የትዳርን ምንነት አስቀድመው ሊያውቁ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ስለ ሥርዐተ ተክሊል አስቀድመው በንስሐ አባታቸው ወይም ሰንበት ት/ቤታቸው ሊማሩ ይገባል፡፡

የንስሐ አባት ምስክርነት
ሥርዐተ ተክሊል የሚፈጸምላቸው ወጣቶች አስቀደሙው ንስሐ እየገቡ ንጽሕናቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ የግድ የንስሐ አባት ሊይዙ ያስፈልጋል፡፡ ለንስሐ አባታቸውም ስለጋብቻቸውም ሆነ ስለማንኛውም ሕይወታቸው ሊያማክሩ ይገባል፡፡ በዘመናችን አልፎ አልፎ እንደሚታየው ገንዘብ ከፍዬ ወይም ወደማልታወቅበት ቦታ ሔጄ አገባለሁ እያሉ ተደብቆ ሥርዐተ ተክሊልን መፈጸም አይቻልም፡፡ ተጋቢዎች ከላይ የተጠቀሱትን ማሟላታቸው በንስሐ አባታቸው ሊረጋገጥና ይህም ሊመሰከርላቸው ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የተጋቢዎቹ መንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ኑሮ በንስሐ አባታቸው ፊት የተገለጠ ሊሆን ይገባል፡፡

             እንግዲህ ተጋቢዎች እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች ካሟሉ የተቀደሰው የሥርዐተ ተክሊል ጋብቻ ሊፈጸምላቸው ይቻላል፡፡ በተረፈ ሥርዐተ ተክሊል ከአጽዋማት ቀናት በስተ ቀር በማንኛውም ቀን ሊፈጸም ይችላል፡፡ ሥርዐተ ተክሊልን ለመፈጸም ወሳኙ ነገር የቀናቱ መለያየት ሳይሆን የተጋቢዎቹ ማንነት ነው፡፡

 

‹‹ መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው፡፡ ለመኝታውም ርኩሰት የለውም ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል፡፡ ›› ዕብ ም፥፲፫ ቑ፥፬

 

ምንጭ : አባቶችህን ጠይቅ ይነግሩህማል